በኢትዮጵያ ዘንድሮ 450 ሺህ ሄክታር ላይ ስንዴ በበጋ መስኖ በማልማት ከዕቅድ በላይ ተከናውኗል- የግብርና ሚኒስትሩ

101

ባህር ዳር ፤ የካቲት 25/2014 (ኢዜአ) መንግሥት ከውጭ የሚያገባውን ስንዴ ለማስቀረት እንዲያገዝ በዘንድሮ የበጋ ወራት 450 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ ስንዴ በመስኖ በማልማት ከዕቅድ በላይ መከናወኑን የግብርና ሚኒስትሩ አቶ ዑመር ሁሴን አስታወቁ።
የፌዴራል፣ የክልልና የዞን ከፍተኛ አመራሮች በባህር ዳር ከተማ አስተዳደር ዘንዘልማ ቀበሌ በ300 ሄክታር በኩታ ገጠም የሚለማ የስንዴ ማሳ ጎብኝተዋል።

የግብርና ሚኒስትሩ በጉብኝቱ ወቅት እንደተናገሩት፤  ከውጭ የሚገባውን ስንዴ ለማስቀረት ግብ ተይዞ የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት በትኩረት እየተሰራ ይገኛል።

በዚህም በዘንድሮ የበጋ ወራት 400 ሺህ ሄክታር መሬት ስንዴ  በመስኖ ስንዴ ለማልማት ታቅዶ በተደረገው ጠንካራ እንቅስቃሴ  በመጀመሪያው ዙር 450 ሺህ ሄክታር መሬት በማልማት ከዕቅድ በላይ መከናወኑን   አስታውቀዋል።

ከዚህ ውስጥ ከ40 ሺህ ሄክታር የሚበልጠው በአማራ ክልል የለማ መሆኑን ጠቅሰው፤ ይህም ክልሉ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ሆኖ ያካሄደው ልማት በጦርነቱ የታጣውን ምርት ለማካካስ ያግዛል ብለዋል።

በባህር ዳር የተመለከቱት የስንዴ ልማት  ለከተማ ግብርና  ትልቅ እመርታ መሆኑ ተመልክቷል።

መንግሥት ባስቀመጠው አቅጣጫ መሰረት ሁለተኛውን ዙር የበጋ መስኖ ስንዴን ጨምሮ ዘንድሮ ከግማሽ ሚሊዮን ሄክታር በላይ በማልማት እስከ 20 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለመሰብሰብ መታቀዱን አስረድተዋል።

በቀጣይም ምርቱን ይበልጥ ለማሳደግና ልማቱን ከቴክኖሎጂ ጋር አቀናጅቶ ለማከናወን መንግሥት ትኩረት መስጠቱን   ሚኒስትሩ ገልጸዋል።

የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳደር ዶክተር ይልቃል ከፋለ በበኩላቸው፤ በተያዘው ዓመት ክልሉ በጦርነት ውስጥም ሆኖ ለግብርናው በሰጠው ትኩረት የበጋ መስኖ ስንዴ ልማቱን ውጤታማ እንደሆነ ነው የተናገሩት።

የተከናወነው የበጋ መስኖ ስንዴ ልማትም ክልሉ ካስቀመጠው ዕቅድ አንፃር ገና ብዙ ጥረት የሚጠይቅ ቢሆንም፤ ጅምሩ ተስፋ ሰጪ መሆኑን በተግባር አረጋግጠናል ብለዋል።

መንግሥት የክልሉን ግብርና በቀጣይ ለማዘመንና በኩታ ገጠም እርሻ የሚከናወነውን ልማት ከመካናይዜሽን ጋር ለማስተሳሰር  ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሰራ አስታውቀዋል።

የግብርና ምርታማነትን በሦስት እጥፍ በማሳደግም የሀገራችንን የምግብ ፍጆታን በአጭር ጊዜ በማሟላት ከውጭ የሚገባውን የስንዴ ማስቆም እንችላለን ብለዋል።

ለዚህም በየደረጃው ያሉት አመራሮችና የግብርና ባለሙያዎች ምርታማነትን በማሳደግ በምግብ ራሳችንን ለመቻል የያዝነውን ዕቅድ እንዲሳካ ሊረባረቡ ይገባል ሲሉም ርዕሰ መስተዳድሩ አሳስበዋል።  

ከዚህ ቀደም መሬቱን በክረምት ወቅት በሩዝ ያለሙትን ምርት በማንሳት ቀሪ ርጥበትን ተጠቅመው ለሁለተኛ ዙር የሚያለሙት የጓያ ሰብል በበሽታ ስለሚጠቃ ተጠቃሚ እንዳልነበሩ የተናገሩት ደግሞ የዘንዘልማ ቀበሌ  አርሶ አደር ገዳሙ በሬ ናቸው።

ዘንድሮ በማሳቸው ያለውን ሩዝ አጭዶ በማንሳት የግብርና ባለሙያዎችን ምክር ተቀብለው ለመጀመሪያ ጊዜ ግማሽ ሄክታር መሬት ላይ በበጋ መስኖ ስንዴ ማልማታቸውን አመልክተው፤ ይህም ከራሳቸው የምግብ ፍጆታ ተርፎ ለገበያ በማቅረብ ተጠቃሚ እንደሚሆኑ ያላቸውን ተስፋ ገልጸዋል።

አርሶ አደር ካሱ ጎበዝአየሁ በበኩላቸው፤ ዘንድሮ እያለሙት ያለው ስንዴ በማልማት ቁመናውና የምርት አያያዙ መልካምና  በዚህም ደስተኛ መሆናቸውን ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ በከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ  ከውጭ የምታስገባውን ስንዴ በሀገር ውስጥ በማምረት ለመተካት ጥረት እያደረገች መሆኗን መረጃዎች ያመለክታሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም