የአሰላ ከተማ አስተዳደር ለምሥራቅ ባሌ ዞን በድርቅ ለተጎዱ ወገኖች የምግብ እህል ድጋፍ አደረገ - ኢዜአ አማርኛ
የአሰላ ከተማ አስተዳደር ለምሥራቅ ባሌ ዞን በድርቅ ለተጎዱ ወገኖች የምግብ እህል ድጋፍ አደረገ
ጎባ፤ የካቲት 25/2014(ኢዜአ) የአሰላ ከተማ አስተዳደር በምሥራቅ ባሌ ዞን በተከሰተው ድርቅ ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች አንድ ሺህ ኩንታል የምግብ እህል ድጋፍ አደረገ፡፡
ድጋፉን የአሰላ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ገዛሊ ሃሹ ለምሥራቅ ባሌ ዞን ተገኝተው ባስረከቡበት ወቅት፤ ድጋፉ እኛ ኢትዮጵያዊያን በችግር ጊዜ የመረዳዳትና የመደጋገፍ እሴት ማሳያና ተጠናክሮ የሚቀጥል ነው ብለዋል።
ከተማ አስተዳደሩ ለድርቅ ተጎጂ ወገኖች ያደረገው ድጋፍ ህብረተሰቡን በማስተባበር 3 ነጥብ 7 ሚሊዮን ብር ግምት ያለው 1ሺህ ኩንታል የምግብ እህል መሆኑንም አውስተዋል፡፡
የምስራቅ ባሌ ዞን ምክትል አስተዳዳሪ አቶ መሐመድ ኢስማኤል በበኩላቸው፤ የአሰላ ከተማ አስተዳደር ያደረገልን ድጋፍ ድርቁ በተለይም በዜጎች ህይወት ላይ የከፋ ጉዳት እንዳያስከትል መንግስት እያደረገ የሚገኘውን ጥረት የሚያግዝ ነው ብለዋል፡፡
የአሰለ ከተማ አስተዳደር የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎችን በማስተባበር ላደረገላቸው ድጋፍም በዞኑ ተጎጂዎች ስም አመስግነዋል።
ከዞኑ የሀገር ሽማግሌዎች መካከል አቶ መህሙድ ሁሴን በሰጡት አስተያየት፤ የአሰላ ከተማ ጨምሮ በችግር ጊዜ ከጎናችን ለቆሙ ሁሉ ምስጋናችን የላቀ ነው ብለዋል፡፡
በምስራቅ ባሌ አምስት የአርብቶ አደር ወረዳዎች ውስጥ ብዛት ያላቸው ዜጎች የአየር ንብረት ለውጥ ባስከተለው ድርቅ ተጋላጭ መሆናቸውን ከዞኑ የአደጋ ስጋትና የልማት ተነሺዎች ጽህፈት ቤት የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡