ሁለት ሚሊዮን ወጣቶችን ተጠቃሚ የሚያደርግ "ከፍታ" የተሰኘ ፕሮጀክት ይፋ ሆነ

449

የካቲት 25 ቀን 2014 (ኢዜአ) አዲስ አበባን ጨምሮ በ18 ከተሞች ሁለት ሚሊዮን ወጣቶችን ተጠቃሚ የሚያደርግ "ከፍታ" የተሰኘ የተቀናጀ የወጣቶች ልማት ፕሮጀክት ይፋ ተደረገ።

ፕሮጀክቱ ለቀጣይ አምስት ዓመታት የሚተገበር ሲሆን እድሜያቸው ከ15 እስከ 29 ያሉ ወጣቶችን ተጠቃሚ ያደርጋል ተብሏል።

ፕሮጀክቱ በዋናነት ወጣቶች የሕይወት ክህሎትና የሥራ ፈጠራ ሥልጠናዎች እንዲያገኙ ከማድረግ ባለፈ ወጣቶች ሕይወታቸውን ለመቀየር የሚያስችል ድጋፍ ማካተቱ ተገልጿል።   

በሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ በአምሬፍ ኢንተርናሽናልና በሌሎች ተቋማት በጋራ ለሚካሄደው ፕሮጀክት ማስፈጸሚያ 60 ሚሊዮን ዶላር የአሜሪካ መንግሥት ድጋፍ አድርጓል።       

የ"ከፍታ" የወጣቶች የተቀናጀ ልማት ፕሮጀክት ምክትል አስተባባሪ አቶ ዮሴፍ በቀለ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ፕሮጀክቱ በዋነኝነት ሥራ አጥነትን መቅረፍ ነው።

ይህንንም ለማድረግ ፕሮጀክቱ የተለያዩ ተከታታይ የክህሎት ሥልጠና እንደሚሰጥ ተናግረዋል።       

በጤናው ዘርፍ የቤተሰብ እቅድ ሥልጠናዎች መሥጠት ሌላው የፕሮጀክቱ ዓላማ መሆኑን የገለጹት አስተባባሪው፤ የኮምፒዩተር ክህሎት ሥልጠናዎች እንደሚሰጡ አብራርተዋል።  

ተመራቂ ተማሪዎች የሥራ ማመልከቻ አጻጻፍ፣ የሥራ አፈላለግና የሥራ ሥነ-ምግባርን የሚያጎለብቱ የተለያዩ ሥልጠናዎች ይሰጣቸዋል ብለዋል።

የራሳቸውን ሥራ መፍጠር ለሚፈልጉ ደግሞ የሥራ ፈጠራና የገንዘብ አያያዝ የክህሎት ሥልጠናዎች እንደሚሰጡ ተናግረዋል።    

"በወጣቶች የሚመራ ለወጣቶች የሚሰራ ብድርና ቁጠባ ተቋም ማቋቋም የፕሮጀክቱ አንድ አካል ነው" ብለዋል።

በመንግሥት የተገነቡ የወጣቶች ማዕከላትን በማጠናከር ሁሉን አቀፍ ማለትም የሥልጠና፣ የካፍቴሪያና የጤና አገልግሎት የሚሰጥበት ማዕከል ለማድረግ እንደሚሰራ ተናግረዋል።     

የሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ በበኩላቸው ወጣቶች የወደፊቷን ኢትዮጵያ የመገንባት ኃላፊነታቸውን በአግባቡ እንዲወጡ መንግሥት በትኩረት እየሰራ ነው ብለዋል።   

ለዚህም አቅማቸውን የሚገነቡበት ሥርዓት መዘርጋት ወሳኝ መሆኑን አንስተው በዚህ በኩል እንደ "ከፍታ" ያሉ ፕሮጀክቶች አጋዥ መሆናቸውን ነው የገለጹት።       

ፕሮጀክቱ ውጤታማ እንዲሆን ሚኒስቴሩ አስፈላጊውን ድጋፍና ክትትል እንዲሚያደርግም አረጋግጠዋል።

በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ትሬሲ አን በበኩላቸው ፕሮጀክቱ በትግበራው የሁለት ሚሊዮን ወጣቶችን ህይወት እንደሚቀይር ተስፋ አለን ብለዋል።   

ፕሮጀክቱን በይፋ መጀመር አስመልክቶ በወዳጅነት አደባባይ በተካሄደው ሥነ-ሥርዓት ላይ የመንግሥት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎችን ጨምሮ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።

ኢትዮጵያን እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ‼

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም