ኢዜአ የኢትዮጵያን ህልውና በማስቀጠል የቁርጥ ቀን ተቋም መሆኑን በተግባር አሳይቷል- ዶክተር ቢቂላ ሁሪሳ

167

የካቲት 25/2014/ኢዜአ/ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ) የኢትዮጵያን ህልውና በማስቀጠል የቁርጥ ቀን ተቋም መሆኑን በተግባር ማሳየቱን በጠቅላይ ሚኒስትር ፅህፈት ቤት የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ማዕከል አስተባባሪ ሚኒስትር እና የኢዜአ ስራ አመራር ቦርድ አባል ዶክተር ቢቂላ ሁሪሳ ገለጹ።

የኢዜአን የ80 ዓመታት ጉዞ የሚዳስስ የፓናል ውይይት እየተካሄደ ነው።

በፓናል ውይይቱ ላይ ዶክተር ቢቂላ “በሀገር ህልውና ማስከበር ወቅት የኢዜአ ሚና” በሚል ርዕሰ ጉዳይ የመወያያ ፅሁፍ አቅርበዋል።

በፅሁፋቸውም አሸባሪው ህወሓት ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም በሰሜን ዕዝ ላይ የፈፀመውን አሰቃቂ ግፍ ተከትሎ መንግሥት ተገድዶ ወደ ጦርነት ከገባበት ጊዜ ጀምሮ ኢዜአ በግንባር የነበረውን የሚዲያ ዘማችነት ሚና ዳስሰዋል።

ዶክተር ቢቂላ በፅሁፋቸው ኢዜአ በህግ ማስከበርና የኢትዮጵያን ህልውና በማስጠበቅ ተጋድሎ ጉልህ ሚና መጫወቱን አንስተዋል።

በዚህም አሸባሪው ህወሓትና የውጭ ኃይሎች ኢትዮጵያን ለማፍረስ የነበራቸውን ሴራ በማክሸፍ ትልቅ አበርክቶ እንዳለውም ነው የገለፁት።

ኢዜአ ጦርነቱ ከመከሰቱ በፊት መንግሥትና ኢትዮጵያውያን ለሰላም ለአሸባሪው ቡድን ያሳዩትን የሰላም በር በስፋት በመዘገብ የኢትዮጵያን የሰላም እጆች ለዓለም ከፍ አድርጎ አሳይቷል ብለዋል።

ኢዜአ ኢትዮጵያውያን የተደቀነባቸውን አደጋ በቅጡ ተረድተው በህብረ ብሔራዊ አንድነት ለሀገራቸው ህልውና እንዲታገሉ አጀንዳዎችን ከመትከሉ ባሻገር በተለያዩ የጦር ግንባሮች በመገኘት ትኩስ ወቅታዊና ትክክለኛ መረጃዎችን በማድረስ ታሪክ ሰርቷል ነው ያሉት።

የተለያዩ የውጭ ኃይሎችና ሚዲያዎች በኢትዮጵያ ላይ የሀሰት ፕሮፓጋንዳ በከፈቱበት ወቅት ኢዜአ በትክክለኛ መረጃ የፕሮፓጋንዳ ጦርነቱን መመከቱንም ጠቅሰዋል።

በዚህም ኢዜአ የኢትዮጵያን የእውነት ድምፆች በዓለም አደባባይ ከፍ አድርጎ በማሰማት የኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ተቋም መሆኑን አሳይቷል ነው ያሉት።

ኢዜአ ኢትዮጵያዊ አርበኝነት ዳግም በተቀጣጠለበት ወቅት የማይቀረው ድል እንዲመጣ ሚናው ጉልህ ነው ብለዋል።

በድህረ ድል የሰላምና የልማት አጀንዳዎች ላይም ጉልህ ሚና እየተጫወተ መሆኑን አብራርተዋል።

በቀጣይም ሀገር በአጀንዳ እንድትመራ ተቋማዊ ኃላፊነቱን አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አሳስበዋል።