በርዕሰ መስተዳደር ዶክተር ይልቃል ከፋለ የተመራ ቡድን የበጋ ስንዴ ልማት እየጎበኘ ነው

98

ባህር ዳር ኢዜአ የካቲት 25/2014 በአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳደር ዶክተር ይልቃል ከፋለ የተመራና የግብርና ሚኒስትሩ አቶ ኡመር ሁሴን የተገኙበት የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት ጉብኝት በአዊ ብሄረሰብ አስተዳደር በፋግታ ለኮማ ወረዳ ድማማ አንገረፍ ቀበሌ እየተካሄደ ነው።

አመራሮቹና የስራ ሀላፊዎቹ በቀበሌው በ591 ሄክታር ኩታ ገጠም ማሳ ላይ  በመስኖ እየለማ ያለን ስንዴ ጎብኝተዋል።

በዞኑ በበጋ ወቅት ከ12 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በመስኖ ስንዴ እየለማ እንደሚገኝ የብሄረሰብ አስተዳደሩ ዋና አስተዳዳሪ አቶ እንግዳ ዳኘው ገልፀዋል።

በአማራ ክልል ከ40 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በበጋ መስኖ ስንዴ እየለማ መሆኑን መረጃዎች ያሳያሉ።

በጉብኝቱ ርዕሰ መስተዳደሩንና ሚኒስትሩን ጨምሮ የዞን አስተዳዳሪዎች፣ አርሶ አደሮችና ባለድርሻ አካላት እየተሳተፉ ይገኛል።

ጉብኝቱ በምዕራብ ጎጃም ዞን የሚቀጥል ሲሆን በመጨረሻም በከፍተኛ አመራሮች የስራ አቅጣጫ ይሰጣል ተብሎ ይጠበቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም