ኢዜአ እውነትን ከአገር ጥቅም ጋር በማስተሳሰር ለኢትዮጵያ የቀጣይ ጉዞ የሚጠበቅበትን ሃላፊነት ሊወጣ ይገባል

86

የካቲት 25/2014/ኢዜአ/ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ) እውነትን ከአገር ጥቅም ጋር በማስተሳሰር ለኢትዮጵያ የቀጣይ ጉዞ የሚጠበቅበትን ሃላፊነት ሊወጣ ይገባል ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ገለጹ።

የኢዜአ 80ኛ ዓመት በተለያዩ መርሃ ግብሮች እየተከበረ ሲሆን በዛሬው እለትም ዓውደ ርእይ ተከፍቷል የፓናል ውይይትም ይካሄዳል።

በመርሃ ግብሩ ላይ የተገኙት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ባደረጉት ንግግር ኢዜአ በርካታ የሚዲያ ባለሙያዎችን በማፍራት ለኢትዮጵያ የሚዲያ እድገት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረከተ አንጋፋ ተቋም መሆኑን ገልጸዋል።

ዜና የታሪክ መሰረት መሆኑን ጠቅሰው፤ ኢዜአ ያለውን የበርካታ ዓመታት ልምድ ተጠቅሞ ታሪክ የመሰነድ ስራውን እንዲወጣ አሳስበዋል።

ዘላቂ ቋሚና ሀገር አሻጋሪ ተቋማትን መፍጠርና ማጠናከር አሁን ላለው መንግስት ወሳኝ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ኢዜአ በቀጣይ እውነትን ከአገር ጥቅም ጋር በማስተሳሰር ለኢትዮጵያ የቀጣይ ጉዞ የሚጠበቅበትን ሃላፊነት ሊወጣ እንደሚገባም አስገንዝበዋል።

በተቋሙ ያለፉ ባለሙያዎች ለሀገር በጎ ነገሮችን አበርክተዋል በስነ ጽሑፍ ረገድም ጉልህ ድርሻ ማበርከታቸውን ገልጸው፤ ተቋሙ ያለውን ልምድ ተጠቅሞ የሚዲያ ተቋማት እንዲጠናከሩ መስራት እንዳለበትም ገልጸዋል።

“አንጋፋውን ዜና አገልግሎትን ለማክበር የተገኙ አንጋፋ ሰዎችን ለማየት እድል ስላገኘሁ እንኳን ደስ አለን ለማለት እፈልጋለሁ” ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም