188 ሺህ የአሜሪካ ዶላር እና ዩሮ በህገ ወጥ መንገድ ሲያዘዋውር የተገኘው ግለሰብ በቁጥጥር ስር ዋለ

84

አዳማ፤ የካቲት 24/2014 (ኢዜአ) በአዳማ ከተማ 188ሺህ የአሜሪካ ዶላር እና ዩሮ በህገወጥ መንገድ ሲያዘውር የተገኘ ግለሰብ በቁጥጥር ስር ማዋሉን ፖሊስ አስታወቀ።

የከተማዋ አስተዳደር  ፖሊስ መምሪያ የሚዲያና ኮሙዩኒኬሽን  ከፍተኛ ባለሙያ ኢንስፔክተር ወርቅነሽ ገልሜቻ ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ አሽከርካሪ የሆነው ግለሰቡ ገንዘቡን ሲያዘዋወር የተገኘው በቅኝት ላይ በነበሩ የፖሊስ አባላት ነው።

በአዳማ  ዳቤ ሶሎቄ ክፍለ ከተማ ዳቤ ቀበሌ ውስጥ  "ኩርፋ ኬላ" ላይ ትናንት ምሽት በተደረገ ፍተሻ መሆኑንም አክለዋል።  

ኢንስፔክተር ወርቅነሽ እንዳሉት፤ ከገንዘቡ ውስጥ  168ሺህ 150  የአሜሪካ ዶላር ሲሆን ቀሪው 19ሺህ 850ው ዩሮ ነው።

ገንዘቡ ሲዘዋወር የተገኘው የሰሌዳ ቁጥሩ ኮድ 3-20460 ኢት በሆነና ከአዲስ አበባ ወደ ጂቡቲ በመጓዝ ላይ በነበረ ባለተሳቢ ተሽከርካሪ ውስጥ መሆኑን ገልጸዋል።

"ገንዘቡን በህገወጥ መንገድ ከሀገር ለማስወጣት ደብቆ የነበረው  አሽከርካሪም በቁጥጥር ስር ውሎ ምርመራ እየተደረገበት ይገኛል" ብለዋል።

ገንዘቡም  ለኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ገቢ መደረጉን የጠቆሙት ባለሙያዋ፣ ገንዘቡ በኢትዮጵያ ብር በዕለቱ የምንዛሬ ዋጋ ሲተመን ከ9 ነጥብ 6 ሚሊዮን ብር በላይ መሆኑን አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም