አርሶ አደሩን በገበያ ተኮር ምርት በማምረት ተጠቃሚ እንዲሆን እየተሰራ ነው

50

ሐዋሳ፤ የካቲት 24/2014 (ኢዜአ) አርሶ አደሩ የምግብ ዋስትናውን ለማረጋገጥ ከሚያከናውነው የሰብል ልማት ጎን ለጎን በገበያ ተፈላጊ የሆኑ ምርቶችን በማምረት ኢኮኖሚያዊ አቅሙን እንዲያጎለብት ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን የሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ደስታ ሌዳሞ አስታወቁ።

ርዕሰ መስተዳድሩ በክልሉ ሀዋሳ ዙሪያ፣ ሸበዲኖ እና ሎካ አባያ ወረዳዎች በበጋ መስኖ የለሙ የስንዴና የጓሮ አትክልት እርሻዎችን ተዘዋውረው በመጎብኘት ከአካባቢው አርሶ አደሮች ጋር ተወያይተዋል።

ርዕሰ መስተዳደሩ በውይይቱ ወቅት እንዳሉት የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ በተያዘው አቅጣጫ መሰረት አርሶ አደሩ ውሀ ገብ በሆኑ አካባቢዎች በመስኖ በማልማት ተጠቃሚ እንዲሆን እየተሰራ ነው።

ዘንድሮ አርሶ አደሩ የበጋ መስኖ ስንዴ እንዲያለማ በተያዘው አቅጣጫ መሰረት ወደ ስራ መገባቱን አስታውሰው፤ በሁለት ወረዳዎች በ138 ሄክታር መሬት ላይ ለሙከራ የተጀመረው የበጋ መስኖ ስንዴ ልማት ስኬታማ መሆኑን አመልክተዋል።

ሰፋፊ መሬት ባለባቸው አካባቢዎች ተሞክሮውን ለማስፋት አመራሩና የግብርና ባለሙያው በትኩረት ሊሰራ እንደሚገባ አሳስበዋል።

ከስንዴ ልማቱ ጎን ለጎን አርሶ አደሩን በገበያ ተፈላጊ የሆኑ የጓሮ አትክልት በማልማት ተጠቃሚ ለማድረግ የክልሉ መንግሥት እየሰራ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።

በመስኖ ልማት ተሳታፊ የሆኑና ማሳቸው ከተጎበኘአርሶ አደሮች መካከል የሀዋሳ ዙሪያ ወረዳ ነዋሪ የሆነው ወጣት ገዛኸኝ ቃሬ በማህበር በመደራጀት የጓሮ አትክልት እያለሙ መሆናቸውን አመልክቷል።

በማህበሩ በሁለት ሄክታር ማሳ ላይ የለማው ቲማቲም፣ጥቅል ጎመን እና በርበሬ በጥሩ ቁመና ላይ እንደሚገኝ ገልጾ፤ ከምርቱ ሽያጭ ከ200 ሺህ ብር በላይ ገቢ እንደሚጠብቁ ተናግሯል።

ያላቸው ጄኔሬተር አንድ ብቻ በመሆኑ መቸገራቸውን የጠቆመው ወጣት ገዛኸኝ፤ ተጨማሪ አንድ ጄኔሬተር ማግኘት ከቻሉ የተሻለ ምርት ማምረት እንደሚችሉ ገልጿል።

የክልሉ እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ቢሮ ሀላፊ አቶ መስፍን ቃሬ በበኩላቸው በመስኖ ልማት ስራው እያጋጠሙ ያሉ ችግሮችን ለመፍታት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

የመስኖ መሰረተ ለማትን ለማስፋፋት እየተሰራ ባለው ስራ የውሃ መሳቢያና ሌሎች ግብዓቶችን ለማሟላት ጥረት እየተደረገ መሆኑን አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም