የክልሉን የቱሪስት መዳረሻዎች አልምቶ በማስተዋወቅ ለምጣኔ ኃብታዊ ጠቀሜታ ማዋል ይገባል

107

አርባምንጭ፤ የካቲት 24/2014 (ኢዜአ)፡ በደቡብ ክልል ያሉ የቱሪዝም መዳረሻዎችን አልምቶ በማስተዋወቅ ለምጣኔ ኃብታዊ ጠቀሜታ ማዋል እንደሚገባ የክልሉ ቱሪዝም ቢሮ አስታወቀ።

የደቡብ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ያለፉት ስድስት ወራት የሥራ አፈፃፀምና በቀጣይ የትኩረት አቅጣጫዎች ላይ ያተኮረ የውይይት መድረክ በአርባምንጭ ከተማ አካሂዷል።

የቢሮ ኃላፊው አቶ ኃይለማርያም ተስፋዬ በዚህ ጊዜ እንዳሉት ክልሉ የበርካታ ቋንቋዎች፣ ባህሎችና መልክዓ ምድራዊ ገፅታዎች  ባለቤት ነው።

የጎብኚዎችን ቀልብ የሚገዙ የተለያዩ ባህላዊ ክዋኔዎች፣ ህዝባዊ በዓላት፣ ታሪካዊ ቅርሶችና ተፈጥሯዊ መስህቦች እንደሚገኙም ገልፀዋል።

ኃላፊው እንዳሉት ክልሉ የእነዚህ ሁሉ ኃብቶች ባለቤት ቢሆንም ከዘርፉ ባለው ኃብት መጠን ተጠቃሚ መሆን አልቻለም።

የክልሉ ሕዝብና መንግሥት ከዘርፉ ተጠቃሚ እንዲሆን የመስህብ ስፍራዎችን በአግባቡ ማጥናት፣ መዳረሻዎችን ማልማት፣ ማስተዋወቅና ዓለም አቀፍ ገፅታ እንዲኖራቸው ማድረግ ይገባል ብለዋል።

በተለያዩ ወቅቶች የሚከናወኑ ህዝባዊ በዓላትና ባህላዊ ክዋኔዎች የጊዜ ቀመራቸውን በአግባቡ በማጥናትና በመሰነድ  የማስተዋወቅ ሥራ መስራት እንደሚያስፈልግም አቶ ኃይለማርያም ጠቁመዋል።

ጎብኚዎች በክልሉ የሚኖራቸውን ቆይታ በማራዘምም የመስህብ ስፍራዎችን መመልከት እንዲችሉ የመንገድ መሰረተ ልማትን ማሟላት እንደሚገባ ተናግረዋል።

በመስህብ ስፍራዎች መዳረሻዎች የእንግዳ ማረፊያ ሆቴሎችና ሌሎች ባህልን ማስተዋወቅ የሚያስችሉ ሥራዎች ይበልጥ ሊጠናከሩ ይገባዋልም ብለዋል፡፡

ቢሮው በክልሉ የሚጎበኙ ሥፍራዎችና የመስህብ አይነቶችን መረጃ ጎብኚዎች በቀላሉ የሚያገኙበት የአንድሮይድ መተግበሪያ የማበልፀግ ሥራ መጀመሩን አስታውቀዋል።

ቀደም ሲል የጥያ ትክል ድንጋይና የኮንሶ ባህላዊ መልክዓ ምድር በዓለም ቅርስነት መመዝገባቸውን ኃላፊው አስታውሰዋል።

ከዚህም ባሻገር በክልሉ የጌዴኦ ባህላዊ መልክዓ ምድርና የወላይታ ብሔር የዘመን መለወጫ በዓል ጊፋታን በአለም ቅርስነት ለማስመዝገብ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ጠቁመዋል።

የጌዴኦ ዞን ባህልና ቱሪዝም መምሪያ ኃላፊ አቶ ዮሴፍ ማሩ ዞኑ ጎብኚዎችን የሚስቡ የመልክዓ ምድር፣ የባህላዊ ክዋኔዎችና ከ6 ሺህ በላይ ትክል ድንጋዮች  መገኛ ታሪካዊ ሥፍራ እንደሆነ ገልጸዋል።

ከባለድርሻና አጋር አካላት ጋር በመተባበር በዞኑ የሚገኙ መስህቦች የማጥናት፣ የመሰነድና የማስተዋወቅ ሥራ መጀመሩንም ተናግረዋል።

በመስህቦች መዳረሻዎች እንደ መንገድ፣ የአገልግሎት መስጫ ተቋማትና ሌሎች መሠረተ ልማቶችን ለማሟላትም ከዞን አስተዳደርና ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅት እየተሰራ ነው ብለዋል።

የስልጤ ዞን ባህልና ቱሪዝም መምሪያ  ኃላፊ አቶ ሸምሱ ሀጂኑር በበኩላቸው በዞኑ በየዓመቱ በበርካታ ቱሪስቶች የሚጎበኘውን አልከስዬ ጥንታዊ መስጂድ፤ ሀረሼጣና እና አባያ ጨለላቃ ሐይቆች እንደሚገኙ ተናግረዋል።

በሐይቆቹ ዙሪያ በአገልግሎት ሰጪ ተቋማት ግንባታ ላይ መሰማራት ለሚፈልጉ አካላት ቦታ የማዘጋጀትና ለማስተላለፍ የሚያስችሉ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች እየተከናወኑ ነው ብለዋል።

በውይይት መድረኩ ላይ የቢሮው የሥራ ኃላፊዎች፣ ባለሙያዎች፣ የዞንና የልዩ ወረዳ አመራሮችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት መገኘታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም