ድርጅቶቹ በአሸባሪው ህወሓት ለችግር ለተጋለጡ ወገኖች የገንዘብ ድጋፍ አደረጉ

58

ደሴ፣ የካቲት 24/2014 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ ሆርቲካልቸር አምራች ላኪዎች ማህበር እና "ሊንሰን ሮዝ አበባ አምራች ድርጅት" በደቡብ ወሎ ዞን አሸባሪው ህወሓት በለኮሰው ጦርነት ለችግር ለተጋለጡ ዜጎች የ1 ሚሊዮን ብር ድጋፍ አደረጉ፡፡

የኢትዮጵያ ሆርቲካልቸር አምራች ላኪዎች ማህበር አማካሪ አቶ ዮሐንስ አበበ በድጋፉ ርክክብ ሥነስርዓቱ ላይ እንደገለጹት አሸባሪው ህወሓት ባደረሰው ሁለንታዊ ጉዳት ዜጎች ለችግር ተዳርገዋል።

በሽብር ቡድኑ ጉዳት የደረሰባቸውን ወገኖችና የወደሙ ተቋማትን በትብብር መልሶ ማቋቋም እንደሚገባም ተናግረዋል።

ማህበሩም ባለድርሻ አካላትን በማስተባበር ለችግር ለተዳረጉ ወገኖች እንዲውል ዛሬ  የግማሽ ሚሊዮን ብር ድጋፍ ማድረጉን ገልጸዋል።

በመንግስትና ባለድርሻ አካላት በዕለት ደራሽ ምግብ አቅርቦትና በመልሶ ማቋቋም የሚከናወኑ ሥራዎችን ለማገዝ ተጨማሪ ድጋፍ እንደሚያደርጉም አረጋግጠዋል።

የ"ሊንሰን ሮዝ" አበባ አምራች ድርጅት ምክትል ሥራ አስኪያጅ አቶ መካሽ ተስፋዬ በበኩላቸው "ሁሉም ከሚበላውና ከሚለብሰው ቀንሶም የተቸገሩትን መርዳትና ማገዝ የዜግነት ግዴታው ነው" ብለዋል።

ዛሬ በጦርነቱ ችግር ለገጠማቸው ዜጎች የሚውል የግማሽ ሚሊዮን ብር ለደቡብ ወሎ ዞን አስተዳደር ድጋፍ ማድረጉን ገልጸዋል።

"ሁሉንም ችግሮች በጋራ ተቋቁመን የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ማስቀጠል አለብን" ያሉት ምክትል ሥራ አስኪያጁ፣ በድርጅቱ በኩል ተጨማሪ ድጋፍ ለማድረግ በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።

የደቡብ ወሎ ዞን ምክትል አስተዳዳሪ አቶ ተስፋ ዳኜ በበኩላቸው በዞኑ በሽብር ቡድኑ ለችግር ለተጋለጡ ወገኖች የዕለት ደራሽ ምግብ እየቀረበ መሆኑን አስታውቀዋል።

በተጨማሪም በሽብር ቡድኑ የወደሙ ተቋማትን መልሶ ለማቋቋም ባለድርሻ አካላትን በማስተባበር ጥረት እየተደረገ ነው ብለዋል።

አሸባሪው ህወሓት በዞኑ ካደረሰው ሁለንተናዊ ጥፋት አንጻር ተጨማሪ ድጋፍ እንደሚያስፈልግ ገልጸው፤ ሁሉም እያደረገ ያለውን ድጋፍ አጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም