አገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያው ምርታማነትን በማሳደግ የምጣኔ ሃብት እድገት እንዲመዘገብ አስችሏል

438

አዲስ አበባ፣  የካቲት 24/2014(ኢዜአ)  አገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያው ምርታማነትን በማሳደግ በምጣኔ ሃብት እድገት ላይ ተጨባጭ ለውጥ እንዲመዘገብ ማስቻሉን የፕላንና ልማት ሚኒስቴር ገለጸ፡፡

በኢትዮጵያ የኢንዱስትሪ ልማትን በማሳደግ፣ ወደ ውጭ የሚላኩ ምርቶችን ብዝሃነት በማስፋትና ሁሉን አቀፍ እድገት በማምጣት ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ የተዘጋጀ ምክክር በአዲስ አበባ ተካሂዷል፡፡

ምክክሩ በኢንዱስትሪ ሚኒስቴርና የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ንግድና ልማት ኮንፈረንስ በጋራ ትብብር የተዘጋጀ መሆኑም ታውቋል።

በመድረኩ ላይ የተገኙት የፕላንና ልማት ሚኒስትር ዶክተር ፍጹም አሰፋ፤ ኢትዮጵያ የልማት ዕቅዶችን በማዘጋጀት በኩል ከ1957 ዓ.ም የጀመረ የዳበረ ልምድ እንዳላት ገልጸዋል።

በዚህም ፈጣን ኢኮኖሚያዊ እድገት ማስመዝገብ፣ ድህነትን መቀነስና መሰረተ ልማትን ማስፋፋት እንደተቻለ አብራርተዋል።

ኢትዮጵያ እ.ኤ.አ በ2019 የጀመረችው አካታች ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ በተለያዩ ዘርፎች ምጣኔ ሃብታዊ እድገት ማስመዝገብ የሚያስችል መሆኑንም በተግባር አረጋግጠናል ብለዋል።

በኢትዮጵያ ባለፉት ሦስትና አራት ዓመታት በአመራሩ ቁርጠኝነት በመታገዝ በኮቪድ-19 ወረርሽኝም እየተፈተነች ቢሆንም የኢኮኖሚ እድገት ማስመዝገብ መቻሏን ጠቅሰዋል።

በአገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያው ኢንዱስትሪውን በማጎልበት ሁሉን አቀፍ የኢኮኖሚ እድገት ማስመዝገብ የሚያስችል ትክክለኛ አቅጣጫ ላይ እንገኛለን ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያ የተለያዩ ምርቶችን ለውጭ ገበያ ለማቅረብ በአፍሪካ ነጻ የንግድ ቀጣና እና በቻይና መንግስት በኩል የተመቻቸውን ግሪንሌይ የገበያ እድል በአግባቡ ትጠቀምበታለችም ነው ያሉት።

የኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዴኤታ ታረቀኝ ቡሉልታ፤ በኢንዱስትሪው ዘርፍ የአገራዊውን ጥቅል ኢኮኖሚያዊ እድገት ወደ 17 ነጥብ 2 በመቶ ለማሳደግ እቅድ ተይዟል ብለዋል፡፡

የማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ በአገሪቱ የተፈጠረውን የሥራ እድል አምስት በመቶ የያዘ መሆኑን ገልጸው፤ እ.ኤ.አ እስከ 2030  ወደ 15 በመቶ የማሳደግ ትልም አለን ብለዋል፡፡

በተባበሩት መንግስታት ድርጅት በማደግ ላይ ያሉ አገራት ልዩ መርሃ ግብር የአፍሪካ ዳይሬክተር ፖል አኪውሚ፤ ታዳጊ አገራት ኢኮኖሚያዊ እድገት ለማስመዝገብ የምርት ትስስር፣ የሥራ እድል ፈጠራ አቅምና ምርታማ ሃብቶችን መለየት አለባቸው ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያ ከ5 ሺህ ሜጋ ዋት በላይ ኃይል ማመንጨት የሚችለውን ታላቁን የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ጨምሮ በሌሎች ዘርፎች አቅሟን እየተጠቀመች መሆኗን ገልጸዋል፡፡

ኢትዮጵያ ጠንካራ የኢንዱስትሪ ፖሊሲ እንዳላት ጠቅሰው፤  የውጭ ኢንቨስትመንትን በመሳብ መሰረታዊ ለውጥ ማምጣት እንደምትችልም ማሳያ ነው ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም