ትውልዱ በድኅነትና ኋላ ቀርነት ላይ የአድዋን አይነት ድል መቀዳጀት አለበት

58

የካቲት 24 2014 (ኢዜአ) የአሁኑ ትውልድ በድኅነትና በኋላ ቀርነት ላይ የአድዋን አይነት ድል መቀዳጀት አለበት ሲሉ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ገለጹ።

126ኛውን የአድዋ ድል በማስመልከት መቀመጫቸውን አዲስ አበባ ላደረጉ ዲፕሎማቶች፣ ታዋቂ ግለሰቦችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች የእራት ግብዣ ተደርጓል።  

አምባሳደር ዲና በወቅቱ እንደገለጹት፤ የአድዋ ድል የአፍሪካ ድል ነው፤ አለፍ ሲልም የሰው ልጆች እኩልነት የተረጋገጠበት ነው።       

ድሉ የብዝበዛን ቀንበር የሰበረ መሆኑን የተናገሩት ቃል አቀባዩ፤ ነጻነትን ለናፈቁ በቅኝ ግዛት ሥር ለነበሩ አገራት ከፍተኛ መነቃቃት የፈጠረ ድል ነው ብለዋል።   

ከአድዋ ድል ትምህርት የወሰዱ በተጽዕኖ ሥር የነበሩ አገራት ሳያቋርጡ ትግል በማድረግ ድል መቀዳጀታቸውንም ለአብነት ጠቅሰውም የአሁኑ ትውልድ ድህነትና ኋላ ቀርነትን በመታገል ልክ እንደ አድዋ ሁሉ የራሱን ድል ማስመዝገብ ይኖርበታል ሲሉ ገልጸዋል።   

የአድዋ ድል ብዙ የሚያስተምር መሆኑን የገለጹት አምባሳደር ዲና፤ የሰው ልጆች በአንድነትና እኩልነት ላይ የተመረተ ግንኙነት መፍጠር ወሳኝ መሆኑ ልንማርባቸው ከሚገቡ ጉዳዮች መካከል ነው ብለዋል።  

የመርሃ ግብሩ አዘጋጅ አርቲስት ቻቺ ታደሰ በበኩሏ "አድዋ ኢትዮጵያ ቅኝ እንዳትገዛ ያደረገ ድል ብቻ ነው ብሎ የሚያስብ ሰው ሊኖር ይችላል፤ ነገር ግን ድሉ መላ አፍሪካዊያን አሸናፊ የሆኑበት ነው" ብላለች።       

በዕለቱ በተለያዩ ዘርፎች የአፍሪካ ኩራት የሆኑ ሰዎች እውቅና የተሰጣቸው ሲሆን በሴት አመራር ዘርፍ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ እውቅና ሲሰጣቸው በአትሌቲክሱ ዘርፍ ደግሞ አትሌት ኃይሌ ገብረስላሴ እውቅና ተሰጥቶታል።     

በፓን አፍሪካኒዝም ንቅናቄ ደግሞ የቀድሞው የጋና ፕሬዚዳንት ኩዋሚ ንኩርማ እውቅና ከተሰጣቸው መካከል ሆነዋል።  

ኢትዮጵያን እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ‼

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም