ትውልዱ እንደ ጀግኖች አባቶች አንድነቱን ጠብቆ ሀገሩን ማስከበር ይኖርበታል

56

ዲላ ፤የካቲት 22/2014 (ኢዜአ) ወጣቱ ትውልድ እንደ ጀግኖች አባቶች አንድነቱን ጠብቆ የሀገሩ ሉአላዊነትን ከማስከበር ባለፈ ልማትና እድገትን ለማረጋገጥ የድርሻውን መወጣት እንደሚኖርበት ተመለከተ።

126ኛው የአድዋ ድል በዓልን በማስመልከት ኢዜአ ያነጋገራቸው ምሁራን እንዳሉት፤ የድል በዓሉ ሂደት  ጀግኖች  አባቶች ለሀገር ክብር የከፈሉትን መስዋትነት በማሰብ ጭምር ሊሆን  ይገባል።

ጀግኖች አባቶች በጠንካራ አንድነትና ሀገራዊ ወኔ ወራሪውን ሃይል በመመከት ነጻ ሀገርን አስረክበውናል።

ዩኒቨርሲቲ ኦፍ ሳውዝ አፍሪካ የልማት ጥናት የሶስተኛ ዲግሪ  ተማሪና የታሪክ ምሁር  ጸጋዬ ታደሰ ፤ ጀግኖች አባቶች  ከራስ በላይ ሀገርን በማሰቀደም ለኢትዮጵያ ክብር   መስዋዕትነት መክፈላቸውን አስታውሰዋል።

ትውልዱ እንደ አባቶች  አንድነቱን ጠብቆ ለሀገሩ ሉአላዊነት መከበር ቅድሚያ ከመስጠት ባለፈ ልማትና እድገት ለማረጋገጥ የድርሻውን መወጣት አደራ እንዳለበት ተናግረዋል።

የአድዋ ድል በግንባር ተፋልሞ ከማሸነፍ ባሻገር  የጥቁር ህዝቦች ጭቆናንና አይችሉም የተባለውን  የተሳሳተ አስተሳሰብ የሰበረ መሆኑንም  አስረድተዋል። 

ምዕራባዊያን በግንባር ያላዋጣቸውን የቀኝ  አገዛዝ በእጅ አዙር ለማስፈጸም እየሞከሩ እንደሆነ  የገለጹት ደግሞ በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት በታሪክ መምህርነት  ያገለገሉት አሁን በዲላ ከተማ የሚኖሩት አቶ ዱርኦ ጉባ ኡርኦ ናቸው።

ትውልዱ የአድዋን በዓል ሲያከብር ቀደምት አባቶች በግንባር ተፋልመው የከፈሉትን መስዋትነትና ያስረከቡንን ነጻ ሀገር በሚመጥን አስተሳሰብ ማጎልበትና ለተግባራዊነቱ በመዘጋጀት የድርሻችንን መወጣት ይኖርብናል ሲሉ ገልጸዋል።

ወጣቱ ትውልድ በየተሰማራበት የስራ መስክ የነቃ ተሳትፎ በማድረግ የበለጸገች ሀገርን በመፍጠር የአባቶቹን አደራ መጠበቅ እንዳለበት  አመላክተዋል ።

የዲላ ዩኒቨርሲቲ ምርምርና ቴክኖሎጅ ሽግግር ምክትል ፕሬዚዳንት ጽህፈት ቤት ሃላፊ ዶክተር አለማየሁ አካሉ በበኩላቸው ፤ ቀደምት አባቶች ከሀገሪቱ አራቱም ማዕዘናት ተጠራርተው በአንድነት በመሰለፍ  በአድዋ የከፈሉት መስዋትነት ለሀገራቸው ካላቸው ፍቅርና ክብር መሆኑን ተናግረዋል።

ትውልዱም ይህንን በመጠበቅ የሀገሩን ልማትና ብልጽግና ለማረጋጋጥ የድርሻውን መወጣት እንዳለበት አመልክተዋል።

ዶክተር አለማየሁ እንዳሉት፤ በተለይ አባቶች የውስጥ ልዩነቶቻቸውን ወደ ጎን ትተው ሀገራቸውን ለመውረር የመጣውን ጠላት በጋራ ለመመከት ያደረጉት መቻቻልና ለሀገር ልዕልና ያሳዩት የስነልቦና ጥንካሬ ፈተናዎችን ለመሻገር ትልቅ  ትምህርት የሚሆን ነው።

ትውልዱ ከዚህ በመማር ሀገሩን ከመጠበቅ ባለፈ ድህነትን ለማጥፋት በሙሉ አቅሙ በመነሳት የአባቶችን አደራ መወጣት እንዳለበት ነው የተናገሩት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም