መድረኩ የተሳሳቱ የፖለቲካና የታሪክ አረዳዶችን በማስወገድ ብሔራዊ እርቅን ለማምጣት ያግዛል

74

ባህር ዳር (ኢዜአ)፣ የካቲት 21/2014----አገራዊ የምክክር መድረኩ የተሳሳቱ የፖለቲካ አስተምህሮዎችና የታሪክ አረዳዶችን በማስወገድ ብሔራዊ እርቅን ለማምጣት እንደሚያግዝ የአማራ ክልል ሰቪክ ማህበራት ሕብረት አስታወቀ።

ህብረቱ ለአገራዊ ምክክሩ ስኬታማነት  የበኩሉን አስተዋጾ ለማድረግ ዝግጁ መሆኑን ገልጿል።

አገራዊ የምክከር መድረኩን አስመልክቶ ኢዜአ ከአማራ ክልል የሲቪክ ማህበራት ህብረት አመራሮች ጋር ቆይታ አድርጓል።

የህብረቱ አደራጅ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ማስረሻ ካሣው እንዳሉት ቀደም ሲል በነበረው ህብረ-ብሔራዊነት ትክክለኛ አንድነት ሳይሆን ልዩነቶች ይበልጥ እንዲጎሉ ይደረግ ነበር።

ህወሓት በበላይነት አገር በመራበት ወቅት ከአገራዊ እንድነት ይልቅ በተሳሳቱ ትርክቶች ምክንያት አለመግባባቶች ጎልተው መቆየታቸውን ሰብሳቢው ተናግረዋል።

ከወሰን፣ ከህገ-መንግስት፣ ከማንነት፣ ከባንዲራና ከሌሎችም ጋር በተያያዘ አለመግባባቶች ጎልተው መቆየታቸውን አመልክተዋል።

"በዚህም በአገሪቱ በተለያዩ አካባቢዎች የእርስ በእርስ ግጭት፣ መፈናቀል፣ ጦርነትና መሰል አገራዊ ሳንካዎች አጋጥመዋል" ብለዋል።

በተለይም በአንዳንድ የአገሪቱ አካካቢዎች ከኢትዮጵያውያን ባህልና ወግ ያፈነገጡ ተግባራት ጭምር መፈጸማቸውን አስታውሰው፣ ችግሩን በሰከነ አግባብ ተነጋግሮ ለመፍታት አገራዊ ምክክሩ ወሳኝና አሻጋሪ መሆኑን ተናግረዋል።

"ሕብረቱ አገራዊ የምክክር መድረኩ የተሳሳቱ የፖለቲካ አስተምህሮዎችና የታሪክ አረዳዶችን በማስወገድ ብሔራዊ እርቅ ያመጣል ብሎ ያምናል" ሲሉም ገልጸዋል።

አቶ ማስረሻ እንዳሉት ለአገራዊ ምክክሩ ስኬታማነት የአማራ ክልል ሲቪክ ማህበራት ሕብረት የበኩሉን አስተዋጽኦ ለማድረግ ዝግጁ ነው።

ለውይይት የሚጠቅም አጀንዳ መርጦ በማቅረብና አጀንዳዎች ከፍተኛ ውይይት እንዲደረግባቸው በማድረግ በኩል ከሲቪክ ማህበራት ሰፊ ሚና እንደሚጠበቅ ተናግረዋል።

በሚቀርቡ አጀንዳዎች ላይ ህዝባዊ ውሳኔዎች ሊኖሩ እንደሚችሉ ጠቁመው፣ ሕብረቱ ህዝብን ተጠቃሚ በሚያደርግ መልኩ አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግ መዘጋጀቱን ጠቁመዋል።

ሕብረቱ ከማንኛውም የፖለቲካ ፓርቲ አስተሳሰብ ነጻ በሆነ መልኩ በታዛቢነት ጭምር በመሳተፍ ለአገራዊ ምክክሩ ስኬታማነት አንደሚሰራ አረጋግጠዋል።

"አገራዊ የምክክር መድረኩ አገር አሁን ከገጠማት ውስብስብ ችግር እንድትላቀቅ በማድረግ በኩል አስፈላጊነቱ አጠያያቂ አይደለም" ያሉት ደግሞ የህብረቱ ቁጥጥርና ኦዲት ሰብሳቢ አቶ ዓለምአየሁ ፈንታ ናቸው።

'በብሽሽቅና በመገፋፋት የሚመጣ መፍትሄ እንደሌለ ጠቁመው፣ መድረኩ ለኢትዮጵያዊያን ትልቅ እድል መሆኑን ተናግረዋል።

ብሔራዊ ምክክሩን እንዲመሩ የተመረጡ ኮሚሽነሮች የኢትዮጵያን ችግር የሚረዱና በገለልተኝነታቸውም እንደማይጠራጠሩ ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ ብሔራዊ መግባባትን ለመፍጠር አገራዊ የምክክር ኮሚሽን እንዲቋቋም መደረጉ የሚታወቅ ነው።

በቅርቡም የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባካሄደው ሁለተኛ አስቸኳይ ጉባኤ የኮሚሽኑን 11 ኮሚሽነሮች ሹመት ማጽደቁ ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም