የአድዋ ድል ኢትዮጵያውያን አንድ ከሆንን የማንተገብረው ነገር እንደሌለ ማሳያ ነው- የመገናኛ ብዙሀን ባለሙያዎች

120

ሀዋሳ፤ የካቲት 22/2014 (ኢዜአ) የአድዋ ድል ኢትዮጵያውያን አንድ ከሆንን የማንተገብረው ነገር እንደሌለ ማሳያ ነው ሲሉ በሀዋሳ ኢዜአ ያነጋገራቸው የታሪክና የመገናኛ ብዙሀን ባለሙያዎች ገለጹ።
 

አስተያየት ሰጪዎቹ ለኢዜአ እንዳሉት ዳግማዊ  አጼ ሚኒሊክ ለመላው ኢትዮጵያውያን ያደረጉትን የክተት ጥሪ ተከትሎ ኢትዮጵያዊያን  በአንድነት በመዝመት ወራሪውን የኢጣልያ ጦር በመደምሰስ አኩሪ ድል አውርሰውናል።

በታሪክ መምህርነት ለበርካታ አመታት ያገለገሉትና በአሁኑ ወቅት በደቡብ ክልል መንግስት ኮሚኒኬሽን ቢሮ የሚዲያ ሞኒተሪንግ ዳይሬክቶሬት ተወካይ አቶ ዘለቀ ከበደ እንዳሉት በሀገር ጉዳይ የማይደራደሩት ጀግኖች አርበኞች የነበራቸው አንድነት  ወራሪውን ሃይል ለመደምሰስ አስችሏቸዋል።

ለአድዋ ድል በርካታ ምክንያቶች መኖራቸውን የጠቆሙት አቶ ዘለቀ በወቅቱ መላው ኢትዮጵያውያን የሚያምኑትና የሚከተሉት ጠንካራ መንግስት መኖሩን እንደ አንድ ምክንያት አንስተዋል።

"በየአካባቢው የነበሩት ገዥዎች በሀገራዊ ጉዳይ ከዳግማዊ አጼ ሚኒሊክ ጋር ባይስማሙ ኖሮ ህዝቡ ለጦርነቱ አይወጣም ነበር" ብለዋል።

ሌላው ለአድዋ ድል እንደ ምክንያት ያነሱት ጦርነቱ ሀገርን፣ ነጻነትንና ማንነት ላለመቀማት የሚደረግ የፍትህ ጦርነት መሆኑን ኢትዮጵያውያን አምነው መስዋዕትነት ለመክፈል በስነ ልቦና ዝግጁ መሆናቸው እንደሆነ ገልጸዋል።

የህዝቡ ስነልቦና ሰው ከመሆን የመነጨ እንጂ በሌላ ማንነት ላይ ያልተንጠለጠለ መሆኑን ጠቅሰዋል።

ወጉ፣ ባህሉና እምነቱ እንዳይበረዝበት ከመላ ሀገሪቱ ከ100 ሺህ በላይ የሚገመት ኢትዮጵያዊ ስንቁን በመያዝ መዝመቱንና በጽናት በመዋጋቱ ድል ለማድረግ መቻሉን ጠቁመዋል።

ኢትዮጵያውያን የአድዋ ጀግኖች ያደረጉት ተጋድሎና ያስገኙት ድል ሁሌም አብሯቸው የሚኖርና በሀገር ጉዳይ የማይደራደሩ መሆናቸውን በቅርቡ የመንግስትን ጥሪ በመቀበል ለህልውና ዘመቻው ዳር እስከዳር መነሳታቸው ማሳያ እንደሆነ አስረድተዋል።

አንዳንድ ምዕራባዊያን ሀገራት የራሳቸው ባህል፣ ታሪክ፣ ማንነትና ሀብት ያላቸውን ሀገራት ህዝቦች ለመከፋፈል ልዩነትን አጉልቶ እርስ በእርስ ማጋጨት ለእጅ አዙር ቅኝ አገዛዝ ዋነኛ ስልት አድርገው እየሄዱበት መሆኑን ተናግረዋል።

በብሔር፣ በቋንቋ፣ በሰንደቅ አላማና በታሪክ ውዝግብ ውስጥ እንድንገባ የተደረገበት ሁኔታ ለዚሁ ማሳያ መሆኑን  ጠቁመዋል።

"ባለመከፋፈል እንደ ቀድሞ አባቶቻችን አንድነታችንን አጽንተን የኢትዮጵያን አሸናፊነት ዳግም ማሳየት አለብን'' ብለዋል።

"ኢትዮጵያውያን ታሪካችንን ጠንቅቀን በማወቅ አንዳንድ ምእራባዊያን ከሰጡን አጀንዳ ወጥተን ሀገራዊ አንድነታችንን በማጠናከር በጋራ መቆም ከቻልን ሁሉንም ማሸነፍ እንችላለን" ነው ያሉት።

ሌላው አስተያየት ሰጪ ጋዜጠኛና የታሪክ መምህር አቶ ሰርካለም አለማየሁ በበኩላቸው የአድዋ ድል በአካል የኢትዮጵያዊያኖች ቢሆንም በመንፈስ ደግሞ የመላው ጥቁር ህዝቦች የድል በዓል ነው።

''አባቶቻቸን እልህ አስጨራሽ ትግል በማድረግ የቀኝ ገዥዎችን አፍሪካን የመቀራመት ተስፋ በማምከን በነጻነት የምንኖርባትን ሀገር አቆይተውልናል'' ብለዋል።

በጀግኖቹ የኢትዮጵያ ልጆች አሸናፊነት የተገኘው ድል የኢትዮጵያዊያን  ብቻ ሳይሆን የመላው ጥቁር ህዝቦች በመሆኑ በአፍሪካ ደረጃ ሊከበር እንደሚገባው ጠቁመዋል።

የአድዋ ድል  በደማቅ ቀለም የተፃፈው በአድዋ ተራሮች ግርጌ ወራሪውን ሃይል ለመመከት በተሰለፈው መላው ኢትዮጵያዊ መሆኑን የገለጹት አቶ ሰርካለም፤ አንዳንድ የምዕራባውያን ሀገራት በፈጠሩት የመከፋፈያ አጀንዳ እርስ በእርስ በመጋጨት ድሉን ማደብዘዝ እንደማይገባ ጠቁመዋል።

''አንድ ስንሆን እጅግ ዘመናዊ መሳሪያ የታጠቀውን የኢጣሊያን ወራሪ ማሸነፍ ችለናል'' ያሉት ጋዜጠኛና የታሪክ ተመራማሪው የአድዋ ድል ጀግና ህዝብ መሆናችንን ብቻ ሳይሆን አንድ ከሆንን የማንተገብረው ነገር እንዳሌለ ማሳያ ጭምር መሆኑን አስረድተዋል።

አድዋ ከኢትዮጵያ ባለፈ የመላው አፍሪካውያንና የጥቁር ህዝቦች ድልም በመሆኑ ይህ ድል በተገቢው መልኩ አፍሪካዊ እንዲሆን ለማድረግ በትኩረት መሰራት እንዳለበት ጠቁመዋል።

126ኛው የአድዋ ድል በዓል በነገው እለት በመላው ሀገሪቱ በተለያዩ ዝግጅቶች ተከብሮ ይውላል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም