አገራዊ ምክክሩ ለዜጎቿ የምትመች አገር ለመፍጠር ያስችላል- ምሁራን

61

ሐረር፣ የካቲት 22/2014(ኢዜአ) ሊካሄድ የታሰበው አገራዊ ምክክር ለዜጎቿ የምትመች አገር ለመፍጠር ያስችላል ሲሉ የሐረማያ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን አመለከቱ፡፡

ለአገራዊ ምክክር ኮሚሽን ተልዕኮ ስኬታማነት የሕዝቡ፣ የመንግሥትና የተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች አስተዋፅኦ ወሳኝ መሆኑን አመልክተዋል፡፡

ኢዜአ ያነጋገራቸው የዩኒቨርሲቲው ምሁራን እንደተናገሩት አገራዊ ምክክሩ በህዝቦች መካከል ያሉ ፍላጎቶችና አመለካከቶችን ለማቀራረብና የሀገሪቱን ሰላም፣ ልማትና ለህዝቦች አብሮነት መረጋገጥ ያግዛል፡፡

የዩኒቨርሲቲው አካዳሚክ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር መንግሥቱ ኡርጌ ዜጎች በአንዳንድ የህገ-መንግሥቱ አንቀጾች ፣ በሰንደቅ ዓላማ፣ በድንበር እንዲሁም እየተተገበረ ባለው ፌደራሊዝም ላይ የተለያዩ አመለካከቶችና ፍላጎቶች እንዳሏቸው ገልጸዋል፡፡

"በመሆኑም እነዚህንና ሌሎች የሀገርን ህልውና እስከ መገዳደር የደረሱ ችግሮችን ለመፍታትና በህዝቦች መካከል ያሉ ፍላጎቶችና አመለካከቶችን ማቀራረብ ያሻል" ብለዋል።

በምክክሩ ሁሉንም ህዝብ በማሳተፍና በጥናት በመታገዝ ብሔራዊ መግባባት ላይ መድረስ እንደሚያስፈልግ ፕሮፌሰር መንግሥቱ አመልክተዋል፡፡

የኮሚሽኑ አባላትም በገለልተኝነትና ከቡድን ፍላጎት ነጻ ሆነው መሥራት እንደሚጠበቅባቸው ገልጸዋል።

"ኮሚሽኑ ሥራውን ከየትኛውም አካል ተጽዕኖ በፀዳ መልኩ እንዲያከናውን እገዛ ሊደረግለት ይገባል" ሲሉ አመልክተዋል፡፡

ዜጎች በሀገሪቱ ለዘመናት ከቆየችባቸው ችግሮች እንድትላቀቅ ተሳትፎ ማድረግ እንደሚጠበቅባቸው ያመለከቱት ምሁሩ፤ "ምክክሩን ስኬታማ ለማድረግ መተባበር ይገባል" ብለዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲው የድህረ ምረቃ ፕሮግራም ዳይሬክተር ዶክተር ፈየራ ዲንሳ በበኩላቸው ምክክሩ ቅራኔዎች እንዲወገዱና መግባባት እንዲጎለብት ከማድረግ አንፃር አዲስ ምዕራፍ ይዞ መምጣቱን ተናግረዋል፡፡

"ምክክሩ ዜጎች በእኩልነትና በትብብር የሚኖሩባትና የምትመች ሀገር ለመፍጠር እንዲሁም ሀገር እንደ ሀገር እንድትቀጥል ጉልህ አስተዋፅኦ ይኖረዋል" ብለዋል፡፡

ምክክሩ የሀገሪቱ ሰላም፣ ልማትና ዴሞክራሲ እንዲዳብር ከማስቻል ባለፈ ቅራኔዎችን በመግባባት በመቀየር አብሮነትና ትብብርን ያጠናክራል ብለው እንደሚያምኑ ገልጸዋል፡፡

ከዚህ ጋር ተያይዞ በዘርፉ የሌሎች ሀገሮች ተሞክሮ መቀመር እንደሚያስፈልግ ዶክተር ፈየራ አመልክተዋል፡፡

"ኮሚሽኑ ሥራውን በገለልተኝነትና በነፃነት እንዲያከናውን ህዝቡ፣ ተፎካካሪ ፓርቲዎችና መንግሥት ትብብር ሊያደርጉለት ይገባል" ብለዋል።

አገራዊ መግባባት ለመፍጠር 11 አባላት ያሉት ኮሚሽን ባለፈው ሳምንት መቋቋሙ ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም