የንፁህ መጠጥ ውሀ እጥረት በእለት ኑሯችን ላይ ጫና ፈጥሮብናል- የሻሸመኔ ከተማ ነዋሪዎች

77

ሻሸመኔ ፣የካቲት 22/2014/(ኢዜአ) የንጹህ መጠጥ ውሀ እጥረት በእለት ተእለት ኑሯችን ላይ ጫና ፈጥሮብናል ሲሉ የሻሸመኔ ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ።

የከተማውን የውሀ እጥረት ለማቃለል በ60 ሚሊዮን ብር የተጀመረ የማስፋፊያ ግንባታ በመጠናቀቅ ላይ መሆኑን አስተዳደሩ አስታውቋል ።

በከተማዋ የቀበሌ 03  ነዋሪ ወይዘሮ ሶፊያ አሊ ለኢዜአ እንደገለጹት ከዚህ ቀደም በሳምንት አንድ ቀን ያገኙ የነበረው የንፁህ መጠጥ ውሀ ስርጭት አሁን ላይ ፈጽሞ እየተቋረጠ በመሆኑ ተቸግረዋል ።

የንጹህ መጠጥ ውሀ አቅርቦት እጥረቱ በመባባሱ ከወንዝ ተቀድቶ በየመንደሩ የሚዞር ውሀ 25 ሊትር ጀሪካን በ10 ብር እየገዙ ለመጠቀም መገደዳቸውን ገልጸዋል።

"ለውሀ ግዥ ከምናወጣው አላስፈላጊ ወጪ በተጨማሪ ንጽህናው ያልተጠበቀ ውሀ በመጠቀማችን ለውሀ ወለድ በሽታ ተጋልጠናል" ብለዋል ።

በከተማው የቀበሌ 01 ነዋሪ አቶ ሀብታሙ ተመስገን በበኩላቸው የንፁህ መጠጥ ውሀ እጥረቱ ከፍተኛ መሆኑን ገልጸዋል።

የከተማው ነዋሪና ዮዲ ሆቴል ስራ አስኪያጅ አቶ አለሙ አበራ በበኩላቸው ከአዋሳና ከቢሻን ጉራቻ ከተሞች ውሀ ገዝተው በተሽከርካሪ በማስመጣት ለሆቴል አገልግሎት እንደሚጠቀሙ ተናግረዋል ።

ከከተሞቹ የሚያስመጡትን ውሀ ለምግብ ማብሰያነትና ለንጽህና መጠበቂያ የሚጠቀሙ ቢሆንም ለተመጋቢው ደንበኛ የመጠጥ ውሀ ማቅረብ አለመቻላቸውን ጠቁመዋል ።

የመጠጥ ውሀ ማቅረብ አለመቻሉ በራሱ ደንበኞች ዘንድ ቅሬታ በመፍጠር በስራቸው ላይ እንቅፋት እየሆነ መምጣቱን ጠቁመው መንግስት የውሀ እጥረቱ እንዲፈታ አፋጣኝ መፍትሄ እንዲፈልግ ጠይቀዋል ።

የሻሸመኔ ከተማ አቦስቶ ጤና ጣቢያ የውሃና ሳኒቴሽን ባለሙያ ኑር ሁሴን በርግቾ  የከተማው የንፁህ መጠጥ ውሃ ችግር ከሚነገረው በላይ ነው" ብለዋል ።

ህዝቡ ከየት እንደመጣ የማይታወቅ ውሀ ከጋሪ አዟሪዎች እየገዛ በመጠቀሙ ለውሀ ወለድ በሽታ እየተጋለጠ መሆኑን ጠቁመው ወደ ሆስፒታሉ ከሚመጡ ታማሚዎች በአሜባ፣ በኮሌራ፣ በጃርድያና በሌሎች ውሃ ወለድ በሽታዎች  ተይዘው የሚገኙ በርካቶች መሆናቸውን ጠቅሰዋል ።

የሻሸመኔ ከተማ አስተዳደር ውሃና ፍሳሽ አገልግሎት ዋና ስራ አስከያጅ ኢንጂነር ደምሴ ኛሬ የነዋሪዎች ቅሬታ ትክክል መሆኑን ተናግረዋል።

አሁን ላይ አገልገሎት እየሰጠ ያለው የውሀ ተቋም የከተማው ነዋሪ 80 ሺህ በነበረበት ጊዜ የተገነባ መሆኑን ጠቁመው አሁን ላይ የነዋሪው ቁጥር 360 ሺህ ከመድረሱ ጋር ተያይዞ የውሀ እጥረቱ መከሰቱን አመልክተዋል ።

"ከዚህ በፊት 10 ቀበሌ የነበራት ሻሸመኔ ከተማ አሁን ላይ ዘጠኝ የገጠር ቀበሌዎች ወደ ከተማዋ መከለላቸው ደግሞ ችግሩን ይበልጥ አባብሶታል" ብለዋል።

የውሀ እጥረቱን ለማቃለል በአስተዳደሩና በነዋሪው ትብብር በ60 ሚሊዮን ብር የተጀመረ የማስፋፊያ ግንባታ 80 በመቶ ደረጃ ላይ መድረሱን የገለጹት ስራ አስኪያጁ ግንባታው በግንቦት ወር 2014 መጨረሻ ተጠናቆ ስራ እንደሚጀምር ተናግረዋል ።

የማስፋፊያው ግንባታ ተጠናቆ ስራ ሲጀምር ከግማሽ በላይ ለሚሆነው ነዋሪ የንጹህ መጠጥ ውሀ ተደራሽ ማድረግ እንደሚቻል ጠቁመው እጥረቱን በዘላቂነት ለመፍታት አቅጣጫ ተይዞ እንደሚሰራ አስታውቀዋል ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም