የመላው ኢትዮጵያዊ ድጋፍ የተጎዳውን ህዝብ ስሜት ለመጠገንና አገልግሎቶችን ተደራሽ ለማድረግ አስተዋጾ እያደረገ ነው

199

ባህር ዳር የካቲት 21/2014 (ኢዜአ) የመላው ኢትዮጵያዊ ያልተቋረጠ ድጋፍ በአሸባሪው ህወሓት የተጎዳውን የህዝብ ስሜት ለመጠገንና መንግስታዊ አገልግሎቶችን ተደራሽ ለማድረግ አስተዋጾ እያደረገ ሲሉ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ይልቃል ከፋለ አስታወቁ።
የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴርና በሥሩ የሚገኙ አራት ተጠሪ ተቋማት  በአማራ ክልል በጦርነቱ ለተጎዱ ወገኖችና ለተቋማት መልሶ ማቋቋም የሚውል በጥሬ ገንዘብ የ15 ነጥብ 6 ሚሊዮን ብር ጨምሮ የቁሳቁስ ድጋፍ ዛሬ አድርገዋል።

የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ይልቃል ከፋለ በድጋፍ ርክክቡ ላይ እንዳሉት አሸባሪው የህወሓት ቡድኑ በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎችን በወራራ ይዞ በቆየበት ወቅት ከፍተኛ ሰብአዊና ቁሳዊ ውድመት አድርሷል።

አሸባሪው በክልሉ በፈፀመው ወረራ የከፋ ሰብአዊና ቁሳዊ ውድመት ቢያደርስም መላው ኢትዮጵያዊ ከክልሉ ጎን በመሰለፍ ያልተቋረጠ አጋርነቱን  እያሳየ  መሆኑን ገልጸዋል።

“የፌደራል መንግስት ተቋማት፣ የክልል መንግስታት፣ ዳያስፖራውና መላ ኢትዮጵያዊ ጥቃታችንን  ለመጋራት ከጎናችን ተሰልፈው ድጋፍ እያደረጉ ይገኛል” ብለዋል።

መላው ኢትዮጵያዊ አይዟችሁ ከጎናችሁ ነን በሚል በተግባር እያደረገ ያለው ድጋፍ በአሸባሪው ህወሓት የተጎዳውን የክልሉ ህዝብ ስሜት እንዲጠገን እያደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴርና በስሩ የሚገኙ ተጠሪ ተቋማትም ዛሬ ላደረጉት የገንዘብና የቁሳቁስ ድጋፍ ዶክተር ይልቃል ከፍ ያለ ምስጋና አቅርበዋል።

የተደረገው ድጋፍ ህዝቡ ተረጋግቶ አዲስ ሕይወት እንዲጀምርና በመልሶ ማቋቋም ግንባታው ላይ እንዲያተኩር የሚያስችል መሆኑን አመልክተዋል።

የወደሙ የመንግስት ተቋማትን ፈጥኖ በማደራጀት መንግስታዊ አገልግሎትን በተሟላ መልኩ ለህብረተሰቡ ተደራሽ ለማድረግና ልማቱን ለማገዝ አስተዋጾው የላቀ መሆኑን ተናግሯል።

የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስትሯ ወይዘሮ ዳግማዊት ሞገስ በበኩላቸው ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱና በስሩ የሚገኙ ተጠሪ ተቋማት በአሸባሪው ህወሓት ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች ድጋፍ ሲያደረጉ ለመጀመሪያ ጊዜ እንዳልሆነ ተናግረዋል።

ቀደም ሲልም በደሴ፣ በደብረ ብርሃንና በአፋር ክልል በመገኘት ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች ድጋፍ መደረጉን አስታውቀዋል።

ዛሬም በወገኖቻችንና በአገልግሎት ሰጭ ተቋማት ላይ የደረሰውን ጉዳት መልሶ ለመታደግ የሚደረገውን ጥረት ለማገዝ በጥሬ ገንዘብ የ15 ነጥብ 6 ሚሊዮን ብርና የቢሮ ቁሳቁስ ድጋፍ መደረጉን ገልጸዋል።

በአሸባሪው ህወሓት የፈራረሱና የወደሙ ተቋማትን መልሶ ሥራ ለማስጀመር ከተደረጉ የቁሳቁስ ድጋፎች መካከል 48 ዴስክቶፕ ኮምፒዩተር፣ ስምንት ፕሪንተር እንደሚገኙበት  አመልክተዋል።

በተጨማሪም 489 ጠረጴዛ እና ወንሮች እንዲሁም የፋይል ካቢኔትና ሌሎች የቢሮ እቃዎች እንደሚገኙበት ጠቅሰዋል።

“ድጋፉ አጋርነታችንን ለመግለፅ፣ ከጎናችሁ መሆናችንን ለማረጋገጥ ነው” ያሉት ሚኒስትሯ፣ በቀጣይም በመልሶ ማቋቋም የተጀመሩ ሥራዎችን ለማገዝ ድጋፉ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።

በድጋፍ ርክክቡ ላይ የክልሉ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎችና የሚኒስቴር መስሪያ ቤቱና የተጠሪ ተቋማት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።