የአሁኑ ትውልድ በመስዋዕትነት የተረከባትን ኢትዮጵያ ወደ ከፍታ ማሻገር ይጠበቅበታል

97

የካተት 21 ቀን 2014 (ኢዜአ) የአሁኑ ትውልድ ኢትዮጵያ አድዋ ላይ በተከፈለ መስዋዕትነት የፀናች መሆኗን በመገንዘብ አገሪቱን ወደ ከፍታ ማሸጋገር እንደሚጠበቅበት ጋዜጠኛና ደራሲ ጥበቡ በለጠ ተናገረ።

የአድዋ ድል ኢትዮጵያን ቅኝ ለመግዛት የመጣውን የጣሊያን ጦር ድል የተደረገበት በደም የተጻፈ ዘመን ተሻጋሪ የሁሉም ኢትዮጵያዊያን ደማቅ የታሪክ አሻራ ነው።

ይህ ድል ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በዓለም ላይ ሁሉ ለሚኖሩ ጥቁር ህዝቦች ተስፋ ፈንጣቂና ለአፍሪካዊያን የነጻነት እንቅስቃሴም መሰረት የጣለ ክስተት ነው።

ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረገው ጋዜጠኛና ደራሲ ጥበቡ በለጠ እንደገለጸው፤ አድዋ ነፃነትን ለተጠሙ ጭቁን ሕዝቦች ሁሉ ብርሃን የፈነጠቀ ደማቅ ታሪካዊ ድል ነው።

ለድሉ መገኘት አንድነትን ለማፍረስ፣ ባህልና ማንነትን ለመበረዝና አገርንም ለማዋረድ የመጣን ወራሪ ኃይል በትብብር ለመመከት መቆማቸው መሆኑን ይናገራል።

ህዝቡም አፄ ምኒሊክ ያስተላለፉትን የክተት ጥሪ ሳያንገራግር በመቀበልና ወደ ጦር ሜዳ መሄዱ ለዚህ ትልቅ ድል ምክንያት ነው ብሏል።

"ከአገር በላይ ምንም የለም" በማለት ኢትዮጵያዊያኖች የውስጥ ልዩነቶችን ወደጎን በመተው በአንድነት ለጋራ ዓላማ መሰለፋቸው ለድሉ እንዳበቃቸው ገልጿል።

የአሁኑ ትውልድም ቀደምት አያቶቹ የሰሩትን ታሪካዊ የአንድነት ገድል በመመርመር በመስዋዕትነታቸው ያስረከቡትን አገር በአንድነት መንፈስ ወደ ከፍታ ማሻገር እንደሚገባው አስገንዝቧል።

126ኛው የአድዋ ድል "አድዋ ለኢትዮጵያዊያን ኅብረት፤ የአፍሪካ የነፃነት ጮራ" በሚል መሪ ሐሳብ ከዛሬ በተለያዩ መርሃ ግብሮች እየተዘከረ ይገኛል። 

ኢትዮጵያን እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ‼

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም