በሩሲያና ዩክሬን መካከል የተፈጠረው ቀውስ በማደግ ላይ በሚገኙ አገሮች ከፍተኛ ጫና ይፈጥራል

51

የካቲት 21 ቀን 2014 (ኢዜአ) በሩሲያና ዩክሬን መካከል እየተካረረ የመጣው ጦርነት በተለይም በአዳጊ አገራት ላይ ከፍተኛ ጫና ያስከትላል ሲሉ አንድ የኢኮኖሚ ምሁር ገለጹ።

በሩሲያና ዩክሬን መካከል እየተካረረ የመጣው ጦርነት ብዙ መዘዞችን የሚያመጣና በርካታ ጉዳቶችን የሚያስከትል መሆኑን የኢኮኖሚ ምሁሩ ዶክተር ቆስጠንጢኖስ ብሩህተስፋ አመላክተዋል።

ጦርነቱ በሁለቱ አገሮች መካከል የሚካሄድ ቢሆንም ብዙዎችን መነካካቱ እንደማይቀር ጠቅሰው፤ በተለይም በማደግ ላይ ባሉ አገሮች ሊያስከትል የሚችለው ጫና ከፍተኛ ሊሆን እንደሚችል ጠቁመዋል።

በኢኮኖሚው መስክ ሩሲያ ከፍተኛ የነዳጅ ላኪ አገር በመሆኗ ጦርነቱ ሲያስተጓጉለው በሚፈጠረው የዋጋ ንረት ኢትዮጵያን ጨምሮ በርካታ አገራት ተጎጂ እንደሚሆኑ ያስረዳሉ።

በጦርነቱ ሳቢያ በዓለም ገበያ የነዳጅ ምርት በበርሜል ከ100 ዶላር በላይ እያሻቀበ መሆኑን ጠቅሰው፤ ይህም በዓለም ኢኮኖሚ ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ ይኖረዋል ነው ያሉት።

በዚህም ምክንያት በኢትዮጵያ በተለይም በምግብ እና በነዳጅ ምርቶች ላይ ከፍተኛ ጫና ሊያሳድር እንደሚችል ዶክተር ቆስጠንጢኖስ ገልጸዋል።

የሁለቱ ሃገራት ግጭት ኢትዮጵያ ከውጭ በምታስገባው የስንዴ ምርት ላይም ተጽዕኖ ስለሚኖረው ሌሎች አማራጮችን መፈለግ እንደሚገባም ጠቅሰዋል።

ኢትዮጵያ በበጋ ወቅት በመስኖ የምታመርተው የስንዴ ምርት ትልቅ ትርጉም ያለው መሆኑን ጠቅሰው፤ ሌሎች ፈጥነው የሚደርሱ ሰብሎችን በማልማት የምርት መጠንን ማሳደግ ላይ ትኩረት ማድረግ እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል። 

ኢትዮጵያን እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ‼

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም