በተደራጀ የንጥቂያና ዝርፊያ ወንጀል የተጠረጠሩ ግለሰቦች ተያዙ

86

ሶዶ፣  የካቲት 21/2014 (ኢዜአ)   ተደራጅተው የዝርፊያ ወንጀል በመፈጸም የተጠረጠሩ ከ10 በላይ ግለሰቦችን በቁጥጥር ስር ማዋሉን የወላይታ ሶዶ ከተማ ፖሊስ አስታወቀ።

በከተማው ለወንጀል መባባስ አስተዋጾ አላቸው የተባሉ የፖሊስ አመራሮች ላይ እርምጃ መወሰዱን የከተማው አስተዳደር አስታውቋል።

የወላይታ ሶዶ ከተማ ፖሊስ ዋና አዛዥ ምክትል ኢንስፔክተር ደሳለኝ ዘውዴ ለኢዜአ እንደገለጹት በከተማው የንጥቂያና ዝርፊያ ወንጀሎች መባባስ በህዝቡ ዘንድ ቅሬታ እያስነሳ ነው ።

ወንጀሎቹን በህብረተሰቡ ተሳትፎ ለማስቀረት የተቀናጀ ዕቅድ ተዘጋጅቶ ወደ ስራ መገባቱን ተናግረዋል።

ህብረተሰቡን ያሳተፈ የወንጀል መከላከል ስራ በተጠናከረ አግባብ ተግባራዊ እየተደረገ መሆኑን አመልክተዋል።

ባለፉት ሰባት ቀናት የተለያዩ መዋቅሮችን በማሳተፍ በተካሄደ የወንጀል መከላከል ተልእኮ በንጥቂያና ዘረፋ ወንጀል የተጠረጠሩ ከ10 በላይ ግለሰቦች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን አስታውቀዋል።

ተጠርጣሪዎች በተደራጀ መልኩ የተንቀሳቃሽ የእጅ ስልክ፣ ቦርሳ፣ ሞተር ብስክሌትና መሰል ንብረቶችን በመንጠቅና በመዝረፍ ወንጀል የተጠረጠሩ መሆኑን ጠቅሰዋል ።

የወላይታ ሶዶ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ መርክነህ ማለዳ በበኩላቸው ከተማ አስተዳደሩ በህዝብ ዘንድ ቅሬታ ሲያስነሱ የነበሩ የጸጥታ ስጋቶችን ለመከላከል በመዋቅሩ ላይ ስር ነቀል ለውጥ ማምጣት ያስቻለ ግምገማ ማካሄዱን ተናግረዋል።

በግምገማው የተሰጣቸውን ሃላፊነት በአግባቡ ባለመወጣት ለወንጀሎች መባባስ ዋንኛ ምክንያት የሆኑ የፖሊስ አመራሮች ተለይተው እርምጃ የተወሰደባቸው መሆኑን  ገልጸዋል ።

ስድስት የስራ ኃላፊዎች ከኃላፊነታቸው መነሳታቸውንም ለአብነት ጠቅሰዋል ።

ኃላፊዎቹን በህግ አግባብ ተጠያቂ ለማድረግ እየተሰራ እንደሆነም አመልክተዋል ።

የወላይታ ሶዶ ከተማ ሰባት መውጫና መግቢያ መንገዶች ያሉባትና ከፍተኛ የሆነ የንግድ እንቅስቃሴ የሚካሄድበት መሆኑን የገለጹት ከንቲባው "በዚህም የአካባቢው ማህበረሰብ ተጠቃሚ ሆኗል" ብለዋል ።

"የህዝብ ልማትና ተጠቃሚነትን ለማደናቀፍ በዝርፊያና በተለያዩ ወንጀሎች በመሳተፍ ለመጠቀም የሚሹ ሃይሎችን አስተዳደሩ አይታገስም " ሲሉም ከንቲባው አክለዋል ።

የከተማው አስተዳደር የህብረተሰቡን የሰላምና ፀጥታ ሁኔታ አስተማማኝ ለማድረግ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅትና በተደራጀ አግባብ እንደሚሰራ ከንቲባው አስታውቀዋል ።

 "በከተማዋ እየተስፋፋ በመጣው የዝርፊያና መሰል ወንጀሎች በዋናነት ተጠቂዎቹ ሴቶችና አቅመ ደካሞች ናቸው " ያሉት ደግሞ የከተማው ነዋሪ ወይዘሮ ውድነሽ ወርቁ ናቸው ።

ከ15 ቀን በፊት ተንቀሳቃሽ የእጅ ስልካቸውን እንደተዘረፉ ገልጸው አሁን ላይ ሴቶች በቀን ጭምር ተንቀሳቃሽ የእጅ ስልክ፣  ቦርሳና ሌሎች ቀለል ያሉ ንብረቶችን ይዘው መንቀሳቀስ አዳጋች እየሆነባቸው መምጣቱን ጠቁመዋል።

"ወንጀሉ በተደራጀ መልኩ እየተፈጸመ ነው" ያሉት ወይዘሮ ውድነሽ "አስተዳደሩ ወንጀለኞችን ተጠያቂ ለማድረግ አሁን ላይ የጀመረው  ህብረተሰቡን ያሳተፈ የአካባቢ ጥበቃና ውይይት ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል " ሲሉ አመልክተዋል ።

 አቶ መብራቱ ዮሐንስ የተባሉ ነዋሪ በበኩላቸው ከአንድ ወር በፊት ግብይት ፈጽመው እስኪመለሱ ሞተር ብስክሌታቸው ከቆመበት ስፍራ መሰረቁን ተናግረዋል።

በዘርፉ የተሰማሩ ወንጀለኞች ሆን ብለው ተዘጋጅተው ንብረቱን የሚያሸሹና የሚደብቁ በመሆኑ ማግኘት እንዳልቻሉ ገልፀዋል ።

በየቀበሌው ማህበረሰቡን በአደረጃጀት በማሳተፍ ወንጀለኞችን ለመከላከል የተጀመረው ስራ ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ አቶ መብራቱ አመልክተዋል ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም