አገራዊ ምክክሩ የተሳሳቱ ትርክቶችን ለማስተካከል እድል ይፈጥራል-የፖለቲካ ፓርቲዎች

75

የካቲት 21 /2014(ኢዜአ) በአገር አቀፍ ደረጃ የሚካሄደው ምክክር የተሳሳቱ ትርክቶችን ለማስተካከል ሰፊ እድል እንደሚፈጥር የፖለቲካ ፓርቲዎች ገለጹ።

የኢትዮጵያ ዜጎች ለማሕበራዊ ፍትሕ /ኢዜማ/ እና የትግራይ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ /ትዴፓ/ አመራሮች አገራዊ ምክክሩ በመሰረታዊ በሆኑ ጉዳዮች ላይ መግባባት ለመፍጠርና የተሳሳቱ ትርክቶችን ለማስተካከል ትልቅ አስተዋጽኦ አለው ብለዋል።

የኢዜማ የሥራ አስፈፃሚ አባል አቶ ማዕረጉ ግርማ እንደገለጹት፤ አገራዊ ምክክሩ ''መሠረታዊና ዋና ዋና በሚባሉ ሐሳቦች ላይ ሥምምነት ላይ ለመድረስ ያስችላል።

ምክክሩ በሕዝቦች መካከል መቃቃር የሚፈጥሩ ትርክቶችን ለማስተካከልና ትርክቶቹን ተከትሎ የሚከሰቱ የተለያዩ ችግሮችን ለመፍታት እንደሚያግዝ ተናግረዋል።

ምክክሩ ሲካሔድ ሁሉም አካል በሰከነ መንገድና አገርን በሚያሻግር መልኩ በቀረቡ ኃሳቦች ላይ በመወያየት የተሻለች ኢትዮጵያን መገንባት እንደሚገባም አሳስበዋል።

አገራዊ ምክክሩ የታለመለትን ግብ እንዲመታ መንግሥትና ሌሎች ባለድርሻ አካላትን ጨምሮ ኅብረተሰቡም የበኩሉን ሚና እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል።

የትዴፓ ዋና ጸሐፊ ጊዴና መድኅን በበኩላቸው መንግሥት የኅዝብ ጥያቄ የሆነውን አገራዊ ምክክር  እንዲቋቋም ማድረጉ ትልቅ ፖለቲካዊ ጠቀሜታ አለው ብለዋል።

አገራዊ ምክክሩ በአገሪቱ ዘላቂ ሠላም ከማረጋገጥ ባለፈ በአገሪቱ የሚስተዋሉ ችግሮችን በውይይት የመፍታት ባሕልን ለማጎልበት አስተዋጽኦው የጎላ መሆኑንም ገልጸዋል።

በተለይም በትርክቶች ላይ ሰፋ ያለ ውይይት በማድረግ ልዩነቶችን የሚያስታርቅ መፍትሄ በማፈላለግ ረገድ ትልቅ ጠቀሜታ እንዳለው ተናግረው ፓርቲው አገራዊ ምክክሩ ውጤታማ እንዲሆን የበኩሉን ድርሻ ለመወጣት ዝግጅት እያደረገ መሆኑንም ጠቁመዋል።

በኢትዮጵያ በተለያዩ የፖለቲካና የኃሳብ መሪዎች እንዲሁም የኅብረተሰብ ክፍሎች መካከል በመሰረታዊ አገራዊ ጉዳዮች ላይ ያለውን ልዩነት አካታች በሆነ የሕዝብ ምክክር ለማቀራረብ የሚያስችል ገለልተኛ አገራዊ ምክክር ኮሚሽን በአዋጅ ቁጥር 1265/2014 መቋቋሙ ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም