በአብርሆት ቤተ-መጽሐፍት የአድዋን ድል የሚዘክር አውደ-ርዕይ ተከፈተ

61

 የካቲት 21/2014 (ኢዜአ) በአብርሆት ቤተ-መጽሐፍት ለሦስት ተከታታይ ቀናት የሚቆይ የአድዋን ድል የሚዘክር አውደ-ርዕይ ለሕዝብ ተከፈተ።
አውደ-ርዕዩ ከየካቲት 21 እስከ 23 ቀን 2014 ዓ.ም ለሕዝብ ክፍት ይሆናል ተብሏል።

የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ዴኤታ ወርቅነሽ ብሩ እንደገለጹት፤ በአወደ-ርዕዩ ኢትዮጵያዊያን ጀግኖች በአድዋ ለአገር ነጻነት የከፈሉትን ዋጋ ይዘክራል ብለዋል።

በአውደ-ርዕዩ ላይ የአድዋን ጀግኖችን የሚዘክሩ ስዕሎች፣ ፎቶግራፎችና የተለያዩ ተጨባጭ ታሪካዊ ቅርሶች በስፋት እንደሚቀርቡም ነው የገለጹት።

እነዚህ ስዕሎችና ፎቶግራፎች ወጣቱ ትውልድ የዛሬይቷ ኢትዮጵያ እንዴት እንደቆመችና የድሉንም ትክክለኛ መረጃ ለማወቅ እድል ይፈጥራል ነው ያሉት።

ይህም ኅብረተሰቡ የአድዋን ድል በተመለከተ ያለውን መረጃ ለማስፋት እንደሚጠቅም ገልጸው፤ በዘርፉ ጥናት ለሚያድርጉ አካላትም ትልቅ ግብዓት እንደሚሆን ተናግረዋል።   

በሌላ በኩል የአድዋ ድልን በተመለከተ የሚሰራጩ የተሳሳቱ መረጃዎችና ትርክቶችን በትክክለኛ መረጃ ለማስተካከል የሚደረገውን ጥረትም እንደሚያግዝ አስረድተዋል።  

ይህንንም ከግንዛቤ በመውሰድ ኅብረተሰቡ በአውደ-ርዕዩ በመሳተፍ የአገሩን ታሪክና ባህል በመጎበኘት የታላቁን አድዋ በዓል እየተዝናና እንዲዘክር ጥሪ አቅርበዋል።

ሚኒስቴሩ ከአዲስ አበባ ባህል፣ ኪነ-ጥበብና ቱሪዝም ቢሮ፣ ከኦሮሚያ ባህልና ቱሪዝም ቢሮና ከኢትዮጵያ ቅርስ ጥበቃ ባለሥልጣን ጋራ በጋራ በመሆን ነው አውደ-ርዕዩን ያዘጋጀው።

የዘንድሮው 126ኛው የአድዋ የድል በዓል “አድዋ ለኢትዮጵያዊያን ኅብረት፤ ለአፍሪካ የነጻነት ጮራ” በሚል መሪ ሐሳብ በተለያዩ መርሃ-ግብሮች ከዛሬ ጀምሮ መከበር ጀምሯል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም