ዳያስፖራው ከሰብአዊ ድጋፍ በተጓዳኝ ለሀገራዊ ልማት በሚያግዙ የኢንቨስትመንት አማራጮች ላይ እንዲሳተፍ ጥሪ ቀረበ

63

ሠመራ ፤ የካቲት 21/2014(ኢዜአ) ዳያስፖራው ለችግር ለተጋለጡ ወገኖች ከሚያደርገው ሰብአዊ ድጋፍ በተጓዳኝ ለሀገራዊ ልማትና እድገት በሚያግዙ የኢንቨስትመንት አማራጮች ላይ እንዲሳተፍ ጥሪ ቀረበ።

"አንድ ነን ኢትዮጵያ በኤልፔድሮ ቦስ ቤተሰብ" የተሰኘ የዳያስፖራ ማህበር እንዲሁም የመስኖና ቆላማ አካባቢዎች ሚኒስቴር አሸባሪው የህወሃት ቡድን ከአፋር ክልል ላፈናቀላቸው  ወገኖች 10ሚሊዮን ብር የሚገመት  ምግብ ነክና ምግብ ነክ ያልሆኑ  ቁሶች ድጋፍ አድርገዋል።

ድጋፉን የተረከቡት የክልሉ ርዕሰ-መስተዳድር አቶ አወል አርባ እንደተናገሩት፤ በአፋር ክልል በጦርነቱ ምክንያት ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ተፈናቃይ ወገኖች የዕለት ደራሽ እርዳታ ጠባቂ ሆነዋል።

ከግለሰብ ፣ከፌዴራልና ክልል መንግስታት አንዲሁም ተቋማትን ጨምሮ  ሁሉም ኢትዮጵያዊ የሚችለውን ሰብአዊ ድጋፍ በማድረግ ለአፋር ህዝብ ወገናዊ አጋርነቱን አሳይቷል  ብለዋል።

ከዚህም ውስጥ ዳያስፖራው በ"በቃ" ዘመቻ በወገናቸው ላይ የተፈጸሙ ግፎችን ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ በማሳወቅና ያልተገቡ የውጭ ጫናዎችን ከመቃወም ጀምሮ በጦርነት ለተፈናቀሉ ወገኖቹ ሰብአዊ ድጋፎችን በማድረግ ታሪክ የማይረሳው አኩሪ ገድል መፈጸሙን አስታውሰዋል።

በተጨማሪም የተደረገውን ሀገራዊ ጥሪ ተቀብሎ ወደሀገሩ በመምጣትም በጦርነት የተጎዱ አካባቢዎችን ተዘዋውሮ በመመልከት በቀጣይ በመልሶ ግንባታዎችም የራሳቸውን ሚና ለመወጣት የጋራ መግባባት ላይም ተደርሷል ነው ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ።

ዳያስፖራው ለችግር ለተጋለጡ ወገኖች ከሚያደርገው  ሰብአዊ ድጋፍ በተጓዳኝ  እውቀታቸውንና ገንዘባቸውን  በመጠቀም ለክልሉ ብሎም ለሀገር ልማትና እድገት በሚያግዙ  የኢንቨስትመንት አማራጮች ላይ እንዲሳተፍ ጥሪ አቅርበዋል።

ርዕሰ መስተዳድሩ፤ ሰብአዊ ድጋፍ ላደረጉት አካላትም ምስጋና አቅርበዋል።

የመስኖና ቆላማ አካባቢዎች ሚኒስትር ኢንጂነር አይሻ መሀመድ በበኩላቸው፤ በክልሉ ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ሰዎች በጦርነቱ ከቤት ንብረታቸው መፈናቀላቸውን ተናግረዋል።

ሁሉም ሀገር ወዳድ ኢትዮጵያዊ የአፋር ህዝብ ለሀገሩ ሲል  የከፈለውን መስዋዕትነት ታሳቢ ያደረገ ሰብአዊ ድጋፉን  አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አመልክተዋል።

ሚኒስቴሩ አንድነን ኢትዮጵያ በኤልፔድሮ ቦስ ቤተሰብ ማህበር፣ ከወንድም ካሊድ ፍውንዴሽን  በኩል ያሰባሰበውን  10ሚሊዮን ብር የሚገመቱ የተለያዩ  ምግብ ነክና ምግብ ነክ ያልሆኑ  ቁሶችን ድጋፍ ማድረጋቸውን ገልጸዋል።
 
"አንድነን ኢትዮጵያ በኤልፔድሮ ቦስ ቤተሰብ"  የዲያስፖራ ማህበር ተወካይ አቶ አንተነህ ለማ ፤  በማህበራቸው በኩል ያደረጉት ድጋፍ ማህበራዊ የትስስር ገፆችን  በመጠቀም  ከተለያዩ ዳያስፖራዎች የተሰበሰበ ነው ብለዋል።

በቀጣይም ማህበራቸው በክልሉ በጦርነት የተጎዱ የጤናና ትምህርት ተቋማትን  መልሶ ለመገንባት የሚያስችል ፕሮጀክት ቀርጸው ለማገዝ እንደሚጥር አስታውቀዋል።

የማህበሩ አባላትና ሌሎችም ዳያስፖራዎች  ገንዘባቸውንም ሆነ  እውቀታቸውን አስተባብረው በሀገራቸው ዘላቂ ልማት ላይ እንዲሳተፉ የበኩላቸውን እንደሚወጡም ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም