የኑሮ ውድነትን የሚያባብሱ ጫናዎችን ለመቋቋም ምርትን ማሳደግ ይገባል-ምሁራን

78

ሀዋሳ፤ የካቲት 21/2014(ኢዜአ) የኑሮ ውድነትን የሚያባብሱ ጫናዎችን በዘላቂነት ለመቋቋም የተለያዩ አማራጮችን በመጠቀም ምርትን ማሳደግ እንደሚገባ የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን አመለከቱ።

በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የአዋዳ ቢዝነስና ኢኮኖሚክስ ኮሌጅ ዲንና የምጣኔ ሀብት ተመራማሪው ዶክተር ወጌነ ማርቆስ ለኢዜአ እንደገለጹት ኢትዮጵያ በተለያየ መስክ ፈጣን እድገት ለማረጋገጥ  የጀመረችው ጥረት በተግዳሮቶች ውስጥ ሆኖም ውጤት እያስመዘገበ ነው።

አሸባሪው ህወሓት የከፈተውን  ጦርነት ምክንያት በማድረግ የአንዳንድ ምዕራባውያን ሀገራት የእጅ አዙር ፍላጎት እያየለ መምጣቱን ጠቅሰው  "ጫናው ኢኮኖሚው እንዲቀዛቀዝና የኑሮ ውድነት እንዲባባስ አድርጓል" ብለዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ ከሰሞኑ ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች በሰጡት ምላሽ ልማት አንዱ የመንግስት የትኩረት አቅጣጫ መሆኑን ማሳወቃቸውን አስታውሰዋል።

 ''ይህን ጊዜ ለመሻገር ያሉንን አማራጮች በሙሉ በመጠቀም ምርት ማሳደግ ላይ ማተኮር አለብን'' ያሉት ዶክተር ወጌነ፤ በተለይ መስኖን በመጠቀም የግብርና ፍላጎትን ማሟላት የሚያስችል ምርት እንዲሰጥ በልዩ ትኩረት መሰራት እንዳለበት አመላክተዋል።

''የተለያዩ የውሃ አማራጭና ለም መሬት ይዘን ሽንኩርት ጭምር ከውጭ እያስገባን ነው'' የሚሉት ምሁሩ፤ እያንዳንዱ ዜጋ በቁጭትና በወኔ በየአካባቢው ያለውን የልማት አማራጭ በማየት ወደ ተግባራዊ ስራ መግባት እንዳለበት ተናግረዋል።

የምርታማነቱ መጠን ባደገ ቁጥር ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በሀገር ውስጥ ምርት መተካት እንደሚቻል ጠቁመው፤   ወደ ውጭ የሚላክ ምርትን ከፍ በማድረግ ጫናውን መቋቋም የሚችል ኢኮኖሚ መገንባት እንደሚቻል  አመልክተዋል።

''አሁን ላይ መንግስት የማስተባበርና አቅጣጫ የማሳየት ሚናውን እየተወጣ ነው'' የሚሉት ዶክተር ወገኔ፤ የመንግስትን አቅጣጫ በመከተል በተለይም የግሉ ሴክተር ግብርናን ጨምሮ በተለያዩ የልማት አማራጮች ሰፊ ተሳትፎ ማድረግ እንደሚጠበቅበት ተናግረዋል።

ጠንካራ የስራ ባህል ማዳበር፣ የስራ ሰዓት መጨመርና ፍላጎትን መቆጠብም ከዜጎች የሚጠበቁ ወሳኝ ጉዳዮች መሆናቸውን አስገንዝበዋል።

ኢትዮጵያን ለማልማት ዜጎች ከተባበሩ አሁን ላይ እንደ ሀገር የገጠሙትን ተግዳሮቶች መሻገር እንደሚቻል የተናገሩት ደግሞ በዩኒቨርሲቲው የገቨርናንስ ልማት ጥናት ትምህርት ቤት መምህር መሐመድ ይመር ናቸው።

መንግስት ከቅርብ ጊዜ ጀምሮ ግልጽ  ራዕይና ግብ በማስቀመጥ እያሳየ ያለው የማስተባበር ሚና አበረታች መሆኑን ጠቁመው፤ ከሰሞኑ ጠቅላይ ሚኒስትሩ አምስት “D”ዎች በማለት ያስቀመጧቸው የትኩረት አቅጣጫዎች ወሳኝ መሆናቸውን ገልጸዋል።

የትኩረት አቅጣጫዎችን በአግባቡ በመተግበር  የኢኮኖሚ ጫናዎችን  መቋቋም እንደሚቻል የገለጹት ምሁሩ፤ መንግስት በዲፕሎማሲው ዘርፍ ኢኮኖሚውን ይበልጥ ሊያነቃቃ የሚያስችል አማራጭ መከተል እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

ኢትዮጵያዊያን የትኛውም ተግዳሮት ሳይበግራቸው ታላላቅ ልማቶች ማከናወን እንደሚችሉ ገልጸው፤ ለተሻለ ስኬት ከመቼውም ጊዜ በላይ አንድነትን  ማጠናከርና አቅምን መጠቀም እንደሚገባ ተናግረዋል።

ከተለያዩ የባለድርሻ አካላት ተጨማሪ የገንዘብ ድጋፎችን በማፈላለግ በዘላቂነት ልማቱን የሚደግፉ ፕሮጀክቶች ግንባታ ላይ ማተኮር እንደሚገባ አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም