ምክክሩ አገርን ማስቀጠል በሚያስችል መልኩ ሊካሄድ ይገባል ---ምሁራን

50

እንጅባራ (ኢዜአ) የካቲት 21/2014 ሊካሄድ የታሰበው ምክክር የተራራቁ ፍላጎቶችን በማቀራረብ አገርን ማስቀጠል በሚያስችል መልኩ ሊካሄድ ይገባል ሲሉ የእንጅባራ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን አመላከቱ።
በዩኒቨርሲቲው የፌደራሊዝም መምህር ጌታዬ ሙሉጌታ ለኢዜአ እንዳሉት፤ ኢትዮጵያውያን ወደአንድ አስተሳሰብ እንዲመጡና አገር ከገጠማት ችግር እንድትወጣ አገራዊ ምክክሩ ወሳኝ ነው።

በመድረኩ ላያግባቡ ጥቃቅን ጉዳዮችን ወደ ጎን በመተው አገርን ማስቀጠል በሚችሉ ገዥ አጀንዳዎች ላይ መግባባት እንደሚገባ ገልፀዋል።

መምህሩ እንዳሉት ባለመግባባቶች አልፈው ኋላም ወደ መግባባት የመጡ ናይጄሪያ፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ሩዋንዳና ሌሎች አገሮችን ተሞክሮ በመውሰድ የተሻለች ኢትዮጵያ ለመገንባት ሁሉን አካታች ምክክር በማድረግ አገርን ማሻገር ይገባል።

የኢትዮጵያ የፌዴራሊዝም ሥርዓት አተገባበሩን መስተካከል እንዳለበት የጠቆሙት ምሁሩ፤ "ሥርአቱ በክልሎች መካከል ትብብርና ትስስርን የሚያመጣና ለአገራዊ አንድነት አደጋ የማያስከትል መሆን ይኖርበታል" ብለዋል

ምክክሩ ስኬታማ እንዲሆን ሁሉም ባለድርሻ አካላት በሚያግባቡ ዋና ዋና ጉዳዮች ላይ በማተኮር አገርን ማስቀጠል በሚያስችል መልኩ መወያየት እንዳለባቸው አመልክተዋል።   ኮሚሽኑ ያለማንም ጣልቃ ገብነት በነጻነት መንቀሳቀስ እንዳለበት ጠቁመው፣ "ለውጤታማነቱ ሁሉም በቅን ልቦና ሊተባበር ይገባል" ብለዋል።

አሁን እየታየ ላለው መከፋፈል የዳረገው የፖለቲካ ምዕራፍ መቋጫ እንዲያገኝ በሚችሉት አቅም ለማገዝ ዝግጁ መሆናቸውን መምህር ጌታዬ አረጋግጠዋል።

የፖለቲካል ሳይንስ ምሁሩ ረዳት ፕሮፌሰር አገናኝ ከበደ በበኩላቸው እንዳሉት ብሔራዊ የምክክር መድረኩ አገር ከገጠማት ችግር የሚያወጣና የተራራቁ ፍላጎቶችን በማቀራረብ ወደ መግባባት የሚያደርስ እንደሚሆን እምነታቸው መሆኑን አመላክተዋል።

"ህዝብ ከህዝብ ጋር እንዲግባባ፣ የአገር ሰላም እንዲረጋገጥ፣ የእርስ በእርስ ግጭቶችና መፈናቀል እንዲቆም መድረኩ ወቅታዊ፣ ወሳኝና አስፈላጊም ነው" ብለዋል።

እንደ ምሁሩ ገለፀ በታሪክ ሩዋንዳውያን ከእርስ በእርስ ግጭት፤ ደቡብ አፍሪካውያን ከአፓርታይድ በኋላ እንደ አገር አንድ የሚያደርጓቸውን ጉዳዮች በማጉላት ፖለቲካዊ ልዩነቶችን በምክክር ፈትተው ወደ መግባባት የደረሱበት ልምድ ለኢትዮጵያ ተሞክሮ ሊሆን ይገባል።

በመሆኑም ኢትዮጵያውያን አገርን ለመታደግ በውይይቱ የቀደመ የመቻቻልና የመተባበር ባህልን በማጎልበት ሀሳብን በመስጠትና በመቀበል መርህ በቅንነት መሳተፍ እንደሚገባ ገልጸዋል።

መድረኩ አገራዊ ጉዳዮችን ለመለየትና በተለይ በየአካባቢው የወሰንና የማንነት ጥያቄዎችን ታሪካዊ ዳራዎችን መሰረት በማድረግ ለመፍታት ሁነኛ መፍትሄ መሆኑን ፕሮፌሰር አገናኝ ተናግረዋል።

በአማራ ክልልም ከወሰንና ከማንነት ጋር በተያያዘ የሚነሱ ጉዳዮች መፍትሄ ያገኛሉ የሚል እምነት እንዳላቸው ጠቅሰው "በምክክሩ በዋናነት በገዥ አጀንዳዎች ላይ ሊተኮር ይገባል" ብለዋል።

እንደ ምሁሩ ገለጻ በምክክሩ ችግሮች የሚፈቱበት መንገድ ላይ በማተኮር የልዩነት መነሻዎችን ነቅሶ ማውጣትና ወደ አንድ የሚያመጡ ህዝባዊ መፍትሄዎች ማስቀመጥ ያስፈልጋል።

ኢትዮጵያ ውስጥ ባሉ መሠረታዊ አገራዊ ጉዳዮች ላይ ምክክር በማድረግ ብሔራዊ መግባባትን ለመፍጠር ይህንን ሂደት የሚመራና የሚያስተባብር አካል ለማቋቋም የሚያስችሉ የተለያዩ ሥራዎች ሲከናወኑ መቆየታቸው የሚታወስ ነው።

በቅርቡም የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባካሄደው ሁለተኛ አስቸኳይ ጉባኤ የአሥራ አንዱ የአገራዊ ምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነሮች ሹመት መጽደቁ ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም