የኢትዮጵያ አየር ሃይል ከኢትዮጵያ መከበሪያነት ባለፈ የአፍሪካ ሞዴል እንዲሆን በልዩ ትኩረት እየተገነባ ነው

96

የካቲት 20 ቀን 2014 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ አየር ሃይል ከኢትዮጵያ መከበሪያነት ባለፈ የአፍሪካ ሞዴል እንዲሆን በልዩ ትኩረት እየተገነባ መሆኑን የመከላከያ ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ተናገሩ።

ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ፤ በኢትዮጵያ አየር ኃይል ጠቅላይ መምሪያ ለጀግኖች በተከናወነው የሜዳሊያ እና የማእረግ አሰጣጥ ፕሮግራም ላይ በመገኘት ለተሸላሚዎች እንኳን ደስ ያላችሁ ብለዋል።

በዚሁ ጊዜ ባስተላለፉት መልእክትም የኢትዮጵያ አየር ኃይል የሰራዊቱ አንዱ ጠንካራ ክንድና የአገር መከታ መሆኑን ገልጸው፤ በኢትዮጵያ ጠንካራ እና ዘመናዊ የባሕር፣ የምድር እና የአየር ሃይል በመገንባት ላይ መሆኑን ጠቅሰዋል።

የኢትዮጵያ አየር ኃይል ከአፄ ኀይለ ስላሴ ዘመን ጀምሮ በአፍሪካ ሞዴል የነበረ፣ በደርግም የድንቅ ሙያተኞች ባለቤትና ጠንካራ ተቋም እንደነበር አስታውሰዋል።

"በወያኔ ስርዓት ግን አየር ኃይል እንዳልነበረ እንዲሆን ተደርጓል፣ ለስሙ ብቻ የነበረ ተቋም አድርገውት ነበር" ብለዋል።

በወቅቱ የነበረው አገዛዝ አየር ሃይሉን በማዳከም ኢትዮጵያ እንዳትከበር እና በቀደምትነቷ እንዳትቀጥል አድርጎት ቆይቷል ነው ያሉት።

በኢትዮጵያ እውን ከሆነው ለውጥ በኋላ ግን በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ አስተዳደር ልዩ ትኩረት ተሰጥቶት ተቋሙን ወደ ነበረበት ከፍታ የመመለስና አዳዲስ መሰረተ ልማቶችን የማሟላት ስራ ተከናውኗል ብለዋል።

አየር ኃይል የኢትዮጵያ መከበሪያና በአፍሪካም የስልጠና ማዕከል ሆኖ በሞዴልነት የሚጠቀስ ተቋም እንዲሆን በልዩ ትኩረት እየተሰራ መሆኑንም ጠቁመዋል።

በሁለት ዓመታት ውስጥ በተቋሙ ዘመናዊ አደረጃጀት በመፍጠርና በመገንባት የታየው ውጤት ከሚጠበቀው በላይ የተሳካ መሆኑንም አንስተዋል።

ለአየር ኃይሉ ስኬታማ ለውጥ መታየት ለሰሩ የተቋሙ አመራሮችና ሰራተኞች ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ምስጋና አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም