ለአገራዊ ምክክሩ ስኬታማነት መገናኛ ብዙሃን የላቀ ድርሻቸውን ሊወጡ ይገባል

102

የካቲት 20/2014/ኢዜአ/ ለኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ስኬታማነት መገናኛ ብዙሃን የላቀ ድርሻቸውን ሊወጡ እንደሚገባ ኢዜአ ያነጋገራቸው አንጋፋ ጋዜጠኞች ተናገሩ።

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የኢትዮጵያ አገራዊ ምክክር ኮሚሽን ማቋቋሚያ አዋጅ እንዲሁም የ11 ኮሚሽነሮችንም ሹመት ማጽደቁ ይታወቃል።

አገራዊ የምክክር ኮሚሽኑም ለዓመታት ምላሽ ሳያገኙ እየተሸጋገሩ የመጡ ችግሮችን በአሳታፊና ሁሉን አቀፍ ምክክር እልባት እንዲያገኙ ማድረግ መሆኑ ተገልጿል።

በመሆኑም ለአገራዊ ምክክሩ ስኬታማነት የመገናኛ ብዙሃን ሚና የላቀ መሆኑን በሙያው ከ50 ዓመታት በላይ ያገለገሉት መምህርና ጋዜጠኛ ማእረጉ በዛብህ ይናገራሉ።

የምክክሩ ሀሳቦች በህዝብ ዘንድ በአግባቡ እንዲሰርጹ እና ህዝብ እንዲመክርባቸው ለማስቻል ሚዲያ የማይተካ ሚና እንዳለው ያምናሉ።

በመሆኑም የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች ሁኔታዎችን በአግባቡ በመገንዘብ ሚዛኑን የጠበቀ እውነተኛ ዘገባ ማድረስ አለባቸው ብለዋል።

የጋዜጠኝነት ሙያ ህዝብን ማገልገል በመሆኑ የሚዲያዎች ዘገባ ለህዝብና ለአገር የሚበጁ ተአማኒ ዘገባዎችን ማድረስ ይጠበቅበታልም ነው ያሉት።

የአሃዱ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅት ዋና ሥራ አስኪያጅ ጥበቡ በለጠ፤ የመገናኛ ብዙሃን የነቃ ተሳትፎ ለአገራዊ ምክክሩ መሳካት ትልቅ ድርሻ እንዳለው ይናገራል።

የኮሚሽኑን ስራዎች በህብረተሰቡ ዘንድ ለማስረጽም የማይተካ ሚና ስላላቸው ጋዜጠኞች ህግና የሙያ ስነምግባርን ጠብቀው መስራት ይጠበቅባቸዋል ብሏል።

የሚዛን የጋዜጠኞች ሙያ ምሩቃን ማህበር ምክትል ፕሬዝደንት ጋዜጠኛ አዲሱ ቢረዳ፤ በበርካታ ሚዲያዎች ዘንድ በሙያዊ አተገባበር ላይ ክፍተት እንዳለ ይናገራል።

በመሆኑም ለአገራዊ ምክክሩ ውጤታማነት የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች ችግሮችን በማረም ለህዝብ የሚጠቅሙ ዘገባዎችን ተደራሽ ለማድረግ መዘጋጀት አለባቸው ብሏል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም