የሾር ወንዝ ድልድይ ግንባታ በመጓተቱ ምርታቸውን ወደ ገበያ ለማጓጓዝ መቸገራቸውን ነዋሪዎች ገለጹ

77

ሚዛን፤ የካቲት 19/2014 (ኢዜአ)፡በቤንች ሸኮ ዞን ደቡብ ቤንች ወረዳ የሾር ወንዝ ድልድይ ግንባታ በመጓተቱ ምርታቸውን ወደ ገበያ ለማጓጓዝ መቸገራቸውን የወረዳው አንዳንድ ነዋሪዎች ቅሬታቸውን ገለጹ።
 የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል የትራንስፖርት እና መንገድ ልማት ቢሮ በበኩሉ ያልተጠናቀቁ የድልድይ ፕሮጀክቶችን ስራ ለማስጀመር 79 ሚሊዮን ብር በጀት መያዙን አስታውቋል።

በወረዳው የቦተር ቀበሌ ነዋሪ የሆኑት አቶ ዳዊት ሳላ የድልድዩ ግንባታ ተጀምሮ መቋረጡን አመልክተው፤ ይሄም በእሳቸውና በሌሎች የአካባቢው ነዋሪዎች የእለት ተእለት እንቅስቃሴ ላይ ችግር መፍጠሩን ተናግረዋል።

በተለይም በወረዳው በስፋት የሚመረተውን የሙዝ ምርት ወደ ወረዳው ዋና ማዕከል ለማጓጓዝ መቸገራቸውን አስታውቀዋል።

አሁን ላይ ወደ ገበያ አውጥቶ  ለመሸጥ የሚያስችል ምቹ ሁኔታ ባለመኖሩ 200 ብር የሚሸጠውን አንድ የሙዝ ቅርንጫፍ የሚዘውን የሙዝ ምርት በ 20 ብር ለመሸጥ መገደዳቸውን ተናግረዋል።

በተለይ በክረምት ወቅት ወንዙ በከፍተኛ ሁኔታ ስለሚሞላ ምንም አይነት እንቅሰቃሴ ለማድረግ እንደማይቻል ጠቅሰው፤ የሚመለከተው አካል አፋጣኝ መፍትሄ እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል።

ሌላው የአካባቢው ነዋሪ አርሶ አደር ባንታ ግኒስ በበኩላቸው የተለያዩ የግብርና ምርት ቢያመርቱም በድልድይ ችግር ምክንያት ለገበያ ማቅረብ አለመቻላቸውን ተናግረዋል።

ከወንዙ ማዶ የሚገኙ ሦስት ቀበሌዎች የሙዝ፣ ቡና፣ ሰብል እና ቅመማ ቅመም ምርቶችን በከፍተኛ ሁኔታ እንደሚያምርቱ እየታወቀ ለድልድዩ ግንባታ ትኩረት አለመሰጠቱ ቅሬታ እንዳሳደረባቸው አስታውቀዋል።

የድልድዩ ግንባታ በገንዘብ እጥረት ምክንያት መጓተቱን የገለጹት ደግሞ በቤንች ሸኮ ዞን ትራንስፖርት እና መንገድ ልማት መምሪያ የድልድይ ግንባታና ኮንትራት አስተዳደር መሐንዲስ  አቶ ኑሩ ሁሴን  ናቸው።

በቤንች ሸኮ ዞን ተመሳሳይ ችግር ያለባቸው ስድስት ድልድዮች መኖራቸውን  ጠቅሰው፤ ድልድዮቹን ለማጠናቀቅ 14 ሚሊዮን ብር እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።

በጅምር ላይ ለሚገኙ ድልድዮችን በዚህ ዓመት የተመደበው በጀት ዝቅተኛ መሆኑን የገለጹት አቶ ኑሩ፤ ቅሬታ እየተነሳበት ያለው ሾር ወንዝ ድልድይ ግንባታ አፈጻጸሙ 50 በመቶ መድረሱን ተናግረዋል።

ለድልድዩ ግንባታ ከተመደበው 5 ነጥብ 4 ሚሊዮን ብር  እሰካሁን 2 ነጥብ 8 ሚሊዮን ብር ብቻ ክፊያ መፈጸሙን ገልጸዋል።

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል የትራንስፖርት እና መንገድ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ፋጅዋ ሳፒ ስለ ጉዳዩ ተጠይቀው በሰጡት ምላሽ በክልሉ ያልተጠናቀቁ የድልድይ ፕሮጀክቶችን ስራ ለማስጀመር 79 ሚሊዮን ብር በጀት መያዙን ገልጸዋል።

ከሾር ወንዝ ድልድይ በተጨማሪ ተመሳሳይ ችግር ያለባቸው 37 ድልድዮች በክልሉ ውስጥ እንደሚገኙ ጠቁመው፤ ግንበታቸውን ለማጠናቀቅ አቅጣጫ ተቀምጦ ወደ ስራ መገባቱን አመልክተዋል።

በዚህም የህብረተሰቡ ቅሬታ በአጭር ጊዜ ምላሽ እንደሚያገኝ ኃላፊው አቶ ፋጅዋ አስታውቀዋል።

በክልሉ የተለያዩ ዞኖች ተጀመረው ያልተጠናቀቁ ነባር ፕሮጀክቶች ሳይጠናቀቁ ምንም አይነት አዲስ ፕሮጀክቶች እንደማይጀመር ኃላፊው ተናግረዋል።

የሾር ወንዝ ድልድይ ግንባታ በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ይጠናቀቃል ተብሎ በ2010 ዓ.ም  መጀመሩ ተመላክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም