ከ21 ሺህ በላይ ወጣቶች በብሔራዊ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ተሰማርተዋል

126

የካቲት 19 ቀን 2014 (ኢዜአ) በ2013 ዓ.ም. በተጀመረው ብሔራዊ በጎ ፈቃድ የማህበረሰብ ልማት ፕሮግራም ከ21 ሺህ በላይ ወጣቶች በመሳተፍ ላይ መሆናቸውን የሠላም ሚኒስቴር ገለፀ።

የሰላም ሚኒስቴር ያዘጋጀው በሰላም ግንባታ ሥራዎች ዙሪያ ያተኮረ የፌደራል እና የክልል አመራሮች የምክክር መድረክ በቢሾፍቱ ከተማ እየተካሄደ ነው።

በምክክር መድረኩ የተገኙት በሰላም ሚኒስቴር የሚኒስትሩ አማካሪ አቶ ካይዳኪ ገዛኸኝ ሚኒስቴሩ ከተቋቋመለት ዓላማ አንፃር ዘላቂ ሰላምን ለማምጣት ህዝባዊ መሠረት ያላቸው የምክክርና የበጎ ፈቃድ ተግባራትን እያከናወነ መሆኑን ጠቁመዋል።

ዜጎች በሀገራዊ ጉዳዮች በባለቤትነት እንዲወያዩ በህዝብና በመንግሥት መካከል ጠንካራ ግንኙነት እንዲኖር በውይይት የሚያምን ማህበረሰብ ለመፍጠርም አሰራሮች ቀርፆ እየተገበረ መሆኑን አንስተዋል።

የሰላም ግንባታ ስራ የማህበረሰቡን እምቅ ማህበራዊ አቅምን መሠረት ያደረገ አዲስ አቅጣጫ በመከተል ህዝባዊ መሠረት ያለው የሰላም ግንባታና ብሔራዊ መግባባትን የሚያጎሉ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን አብራርተዋል።

ሁለንተናዊ ሰላምን ለማረጋገጥ በአሁኑ ወቅት የሰላም ፖሊሲና ስትራቴጂ ተቀርፆ ለመፅደቅ በሂደት ላይ እንደሆነም ጠቅሰዋል።በ2013 በተጀመሩ የማህበረሰብተ ተኮር ምክክሮች በሲቪል ሰርቫንት ምክክርና በበጎፈቃድ አገልግሎት ውጤቶች እየተመዘገቡ ነው ብለዋል።

በብሔራዊ በጎ ፈቃድ የማህበረሰብ ልማት ፕሮግራምም ተነድፎ እየተተገበረ ሲሆን ወጣቶች ከክልላቸው ውጭ ካለው ማህበረሰብ ጋር ቋንቋ አብሮ የመኖር ባህል እና የስራ ባህል እንዲያዳብሩ በመሠራት ላይ መሆኑንም ተናግረዋል።

የበጎ ፈቃድ አገልግሎቱ ከተጀመረ እስካሁን ባለው ጊዜም ከ21 ሺህ በላይ ወጣቶች ተሳታፊ በመሆን ራሳቸውን በመለወጥ ለሌሎችም ተምሳሌት እየሆኑ ነው ብለዋል።

ለአንድ ቀን በሚቆየው መድረክ የማህበረሰብ ተኮር ምክክርና የሲቪል ሰርቪስ ምክክር ሂደት እና በወጣቶች በጎ ፈቃድ አገልግሎት ሂደት ላይ ውይይት እየተደረገ ነው።

በምክክር መድረኩ ላይ የፌደራል የመንግስት ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች የተለያዩ ክልሎች እና ከተማ አስተዳደሮች የሰላምና ደህንነት ኃላፊዎች ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም