ለኢድ አልፈጥር እና ሸዋል ኢድ በዓላት ወደ ሐረሪ ክልል የሚመጡ እንግዶችን ለመቀበል ዝግጅት እየተደረገ ነው

90

የካቲት 18 ቀን 2014 (ኢዜአ)ለኢድ አልፈጥር እና ሸዋል ኢድ በዓላት ወደ ሀረሪ ክልል የሚመጡ እንግዶችን ለመቀበል ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን የሐረሪ ክልል መንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት ገለጸ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በተለያዩ አለማት የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ኢድ አልፈጥር እና ሸዋል ኢድ በዓል በሀገራቸው እንዲያከብሩ ያስተላለፉትን ጥሪ ተከትሎ ወደ ሀረሪ ክልል የሚመጡ እንግዶችን ለመቀበልና ለማስተናገድ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ነው ክልሉ የገለፀው::

የክልሉ ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት ሀላፊ አቶ ሔኖክ ሙሉነህ እንደገለጹት ለዚህም በክልሉ ከፍተኛ የስራ ሀላፊዎች የሚመራ ግብረሃይል ተቋቁሞ ወደ ስራ ተገብቷል። ወደ ክልሉ የሚመጡ ዲያስፖራዎች አስደሳች ቆይታ እንዲኖራቸው ለማስቻል የክልሉ መንግሥት ከህብረተሰቡ ጋር በመሆን እየተሰራ ነው ብለዋል።

የሚመጡ እንግዶችን በአግባቡ መስተናገድ እንዲችሉ ለማድረግም ከሆቴል ቤቶችና ከአገልግሎት ሰጪ ተቋማት ጋር በቅንጅት እየተሰራ ነው።

በክልሉ በርካታ የቱሪስት መዳረሻዎች እንደመገኘታቸውም መጠን ለጎብኝዎች በቱሪዝም ዘርፉም ቀልጣፋ አገልግሎት መስጠት የሚያስችሉ ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን የጠቆሙት ኃላፊው የእንግዶቹ ወደ ክልሉ መምጣትም የተቀዛቀዘው የቱሪዝም ዘርፍ መልሶ እንዲነቃቃ ከማድረግ አንፃርም ፋይዳ የጎላ ነው ሲሉ ተናግረዋል።

እንግዶቹ በክልሉ በሚንቀሳቀሱባቸው አካባቢዎች ነፃ የትራንስፖርት አገልግሎት እንዲያገኙም ከባለድርሻ አካላት ጋር እየተሰራ መሆኑን ነው ያነሱት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም