የፌደራሊዝም ስርዓትና አተገባበሩ

1502

በሃብቱ ተሰማ /ኢዜአ/

ፌደራሊዝም በህዝቦች መካከል ያለውን መስማማት ፣መግባባት እንዲሁም በሁለቱ የመንግስት እርከኖች ʿ በፌደራልና ክልል ʾ  መንግስታት መካከል ያለውን ብዝሃነትና አንድነት የሚገልጽ ሃሳብ ነው፡፡ ፌደራሊዝም ስልጣንን በፌደራል መንግስትና በክልሎች መካከል ግልጽና በሚያግባባ ሁኔታ የሚከፋፍል የመንግስት ስርዓትም ነው፡፡ የሰው ልጅ ህይወቱን በአግባቡ ለመምራት የሚፈጥራቸው የሳይንስ፣ የባህላና የህግ-ስርአቶች እንደየወቅቱና የእድገት ደረጃ ተለዋዋጭ ናቸው፡፡የህግ-ስርአቶች የህዝቡን ስነልቦናዊ፣ ማህበረሰባዊ እድገት ማሳያና ታሪካዊ መነሻም ናቸው፡፡ የፌደራሊዝም ስርአት ብዝሀነትን በማስተናገድና በሀገራቱ  ለሚነሱ ነባር ጥያቄዎች ምላሽ በመስጠት የተሻለ መሆኑን የዘርፉ ምሁራን ያነሳሉ፡፡ የፌደራሊዝም አወቃቀር ነባራዊ መነሻ ፌደራሊዝም እንደየ ሀገራቱ የሕዝብን መሰረታዊ ጥያቄ ለመመለስ  ይዋቀራል ፤በዚህም የብዝሃነት አምድ የሆኑት ኢትዮጵያ፣ ህንድ፣ ስዊዘርላንድና ናይጄርያ ብሄርን መሰረት አድርገው ማዋቀራቸውን በኮተቤ ሜትሮ ፖሊታን ዩኒቨርሲቲ የስነዜና ስነምግባር መምህሩ ዶክተር አየነው ብርሃኑ አስታውቀዋል። ከኢትዮጵያ ጋር ተቀራራቢ የሆነ ማህበረሰባዊ አወቃቀር ያላት ሲዊዘርላንድ የተለያዩ ቋንቋ ተናጋሪ ማህበረሰቦች  ልዩነትን ከአንድነት ጋር ሳይነጣጠሉ ለመምራት እንዳስቻላት የገለጹት ደግሞ  በሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ የፌደራሊዝምና የህግ ትምህርት ክፍል መምህር አቶ ጌድዮን መዝሙር ናቸው፡፡ ከዚህ በተቃርኖ  ዩጎዝላቪያና አብዛኛው የኮሚኒስት ሀገራት  በቀዘቃዛው ጦርነት ጊዜ ፌደራሊዝምን ቢከተሉም ዴሞክራሲን ከፌደራሊዝም በመነጠላቸው መፈራረሳቸውን ጠቁመዋል፡፡ በፌደራል አርብቶ አደርና ፌደራል ጉዳዮች ሚንስቴር የመንግስታት ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ጣሰው ጀጎ ሀገሮች የሚመርጧቸው የፌደራል ስርአት አወቃቀር ከችግራቸው  በመነሳት ነው፤ የኛም ሀገር ቀደምሲል የነበሩ ኢፍትሀዊ የሃብትና የፖለቲካ ግንኙነትን በማስተካከል የብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦችን ተጠቃሚነት እውን ለማድረግ ተሰርቷል ብለዋል፡፡ ብዝሀነትን ለማስተናገድ  የፌደራሊዝም ስርአት ጠቀሜታዎች ፌደራላዊ የመንግስት አወቃቀር ዘርፈብዙ ጥቅሞች እንዳሉት የማሃበራዊና ፖለቲካል ሳይንስ ተመራማሪዎች ይገልጻሉ፡፡በተለይ ፍትሃዊ ተጠቃሚነትን ከማስፈን አንጻር፣አስተዳደራዊ አገልግሎትን በማሳለጥና በማጠናከር የባህል ቋንቋና ሌሎች ማሃበራዊ መገለጫዎችና ከማሳደግ አንጻር ያለው ምቹ ሁኔታ ተመራጭ ያደርገዋል፡፡ የፌደራሊዝም ስርአት መልካም አስተዳደር በማስፈን ህብረብሄራዊ በሆነ መልኩ ቋንቋና  ባህል እንዲያድግ ምቹ ስርአትን ይፈጥራል፡፡ ዴሞክራሲ እንዲጎለብት ያልተማከለ አስተዳደርን መተግበርና ግጭትን በመቻቻል፤ ልዩነትን ከአንድነት አስታርቆ ለመምራት አይነተኛ የፖለቲካ መስመር እንደሆነ ከረጅም አመታት ግጭት በኋላ ሶማሊያና ኢራቅ መጠቀማቸውን ዶክተር አየነው በማሳያነት ይጠቅሳሉ ፡፡ በአፈጻጸም የታዩ ውስንነቶች ምን ነበሩ ፌደራሊዝም ብዙ ቁጥር ያለው ህዝብ ራስን በራስ የማስተዳደርና የጋራ አስተዳደር መዘርጋትን  ቢያካትትም ተግበራዊነቱን የሚያረጋግጡ የዴሞክራሲ ተቋማት አለመዳበራቸው የፖለቲካ ምስቅልቅል መፍጠሩን የተናገሩት አቶ ጌዲዮን ናቸው፡፡ ይህም ግለስቦችና ፓርቲዎች ፖለቲካን ከሀገር  በላይ አድርገው ማሰባቸውና የፌደራሊዝም ጠቀሜታን   ለህብረተሰቡ ማስተማር አለመቻላቸው  የስርአቱ ሚና በተሳሳተ መንገድ ተተርጉሟል  ነው ያሉት ፡፡ በቋንቋ መደራጀቱ ችግር እንደማይፈጥርም ሲዊዘርላድን በአብነት ያነሱት ምሁሩ የኢትዮጵያን ነበራዊ ሁኔታ በማገናዘብ የህዝብን ስብጥር በአቅምነት ከመጠቀም ይልቅ የየአከባቢው ቋንቋ ተናጋሪዎች ሌላውን ለማግለል መዋሉ የስህተቱ መነሻ እንደሆነም አስረድተዋል፡፡ በኢትዮጵያ ተግባራዊ የሆነው የፌደራሊዝም አወቃቀር ከመሪዎች ባለፈ ህዝቡ የዴሞክራሲ ጥያቄን እንደሚፈታ እውቀት ባለመፈጠሩ ከሀገር ይልቅ የግለሰቦችና የብሄር ጥቅሞች ላይ ተንጠልጥሎ ቀርቷል የሚሉት ደግሞ  ዶክተር አየነው ናቸው፡፡ በኢፌዴሪ ህገ-መንግስት ዜጎች ተዘዋውረው የመስራት መብት ቢኖራቸውም በብዙሀን አስተዳደር መዋቅሩ  ውስጥ ተበታትነው የሚኖሩ ጥቂቶች ሰዎች በምን መልኩ  እንደሚወከሉ በግልጽ የማስፈፀሚያ ሰነድ አለመኖሩ  ለሰብአዊ መብት ጥሰት ማጋለጡን አስረድተዋል፡፡ የፌደራሊዝም ምሁሩ ሜጀር ጄነራል አበበ ፌደራሊዝም በህዝቦች ፍላጎት በብሄር መዋቅሩ  አነስተኛ ቁጥር ያላቸውን ህዝቦች  ጥያቄ ምላሽ ቢሰጥም ዴሞክራሲን ከፌደራሊዝም  ስርዓቱ ነጥሎ መተግበሩ ሰዎች ግዴታን በመርሳት በመብት ላይ ብቻ ማተኮራቸው አልፎ አልፎ ለሚታዩት አለመግባባቶች መንስኤ መሆናቸውን ይጠቅሳሉ፡፡ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የህግና አስተዳደር ትምህርት ክፍል መምህሩ ዶክተር ሲሳይ መንግስቴ በበኩላቸው  በሀገሪቱ ባለፉት ዓመታት የነበረው የፌደራሊዝም አተገባበር እውነተኛ ዴሞክራሲ ላይ የተመሰረተ አለመሆኑን ጠቅሰው፥ ገዥው ፓርቲ ራሱ የሚፈልገውን አቋም ከማራመድ አልፎ የህዝቡን አስተያየት አለማድመጡን አንስተዋል። በሌላ በኩል ተቃዋሚ ኃይሎች በተገቢው ሁኔታ የማይሳተፉበት፣ በጠላትነት የተፈረጁበት ሁኔታ መኖሩ የፌደራሊዝም አተገባበሩ ችግር ላይ እንደነበር ማሳያ ነው ብለዋል፡፡ ምሁራኑ ያነሷቸውን የፌደራሊዝም አፈጻጸም ችግሮች  ለመፍታት ለህብረተሰቡ፣ ለባለድርሻ አካላትና ለክልሎች የአሰልጣኞች ስልጠና መሰጠቱን አቶ ጣሰው ጀጎ ተናግረዋል ፡፡ ይሁን እንጂ ክልሎች በራሳቸው ጉዳይ መጠመዳቸው፣ የቅንጅት መጓደልና የቁሳቁስ እጥረት ህዝቡ ፌደራሊዝምን ተረድቶ  ለችግሬ  የመፍትሄ አንድ አካል ነው ብሎ ለመረዳት አላስቻለውም ብለዋል፡፡ አልፎ አልፎ የሚስተዋሉ የአፈጻጸም ችግሮች መስተዋላቸውና የመንግስታቱን ግንኙነት  የሚመራ ራሱን የቻለ ገለልተኛ ተቋም አለመፈጠሩ ሌላው የስራው እንቅፋት ሆኗል ነው ያሉት፡፡ የፌደራሊዝም ስራዓት በአለማችን ላይ ለረጅም አመታት ተፈትኖ ህብረ ብሄራዊነትን  በማቀፍ የተሻለ ቢሆንም በሀገራችን ያለው እድሜ ጅምርና ሳይንሱን ለህዝብ የማስረጽ የህግ ማእቀፍ  ክፍተት የተፈለገውን ውጤት አላስገኘም ብለዋል፡፡ ለሀገር ልማት ሁሉም የበኩሉን እንዲያበረክት  የሞራል እሴቶችን በማዳበር ልዩነትን በህግ የበላይነት መምራት ያስፈልጋል የሉት ደግሞ ዶክተር ዳኛቸው አሰፋ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፍልስፍና መምህር  ናቸው፡፡ በአምቦ ዩኒቨርሲቲ  የፌደራሊዝም መምህሩ አቶ ስዩም ተሾመ የብሄር፣የቋንቋ፣የእምነትና የሀሳብ  ልዩነት መኖር ተፈጥሯዊ በመሆኑ ይህን የምናስተናግድበት ሂደት ጤናማ መሆን ለሀገራዊ አንድነት መሰረት መሆኑን ነው የገለጹት ፡፡ ይሁን እንጂ ባለፉት ጥቂት አመታት  የመንግስት መዋቅሮች የሚያስተላልፉት መልእክቶች በተገቢው አለመቀረጻቸው   ልዩነትን ወደ ከፋፋይነት በመቀየሩ ፌደራሊዝም ውጤታማ እንዳይሆን እንቅፋ መፍጠሩን ገልጸዋል፡፡ በሌላ በኩል ምሁራን በሀገር ግንባታ ላይ የጋራ መግባባት ለመፍጠር  መንግስት በሚቀርጻቸውን ፓሊሲዎች  ህብረተሰቡ ተአሳታፊ  እንዲሆን ሞያዊ ትንታኔ በማቅረብ የድርሻቸውን አለመወጣታቸው  የፌደራሊዝም ስርአቱ የተነሳበትን ግብ ማሳካት አለመቻሉን ነው ያስረዳሉ  ፡፡ ጽንሰ ሀሳቡን ከተግባር ለማስታረቅ ምን መደረግ ያለበት? ፌደራሊዝሙን ውጤታማ ለማድረግ ምሁራኑ ከፍራቻ በመውጣት ያስተማራቸውን ህዝብ ማስተማር፣ ምርምር በማድረግ ከመንግስት ጋር መስራት እንዳለባቸው ጀኔራል አበባ አስረድተዋል።መንግስትም አሁን የተገኘውን ለውጥ መምራት የሚያስችል አሰራር በመዘርጋት ከህዝብና ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር በመወያየት ለመጪው  ምርጫ መሰረት መጣል እንደሚያሥፈልግ ገልጸዋል፡፡ የፌደራሊዝም ስርዓቱን ለማጠናከር የሀሳብ ብዝሃነትን ማካተት፣ የክልሎች አደረጃጀት በጥናትና በውይይት ላይ የተመሰረተ ማድረግ፣ ፍትሐዊ የሃብትና የስልጣን  ክፍፍል ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን ዶክተር ሲሳይ ተናግረዋል። ምሁራን ለዚህ ስኬታማነት በጥናትና ምርምር እያስደገፉ የለውጡን ስኬትና ክፍተት እየለዩ የፖሊሲ መነሻ ሀሳብ ማቅረብ እንደሚገባቸውም እንዲሁ። የፌደራሊዝምን ስርዓት በአግባቡ ለመምራት የኢኮኖሚ እድገት ፍትሀዊነት የፖለቲካ ምህዳር መስፋትና የውይይት ባህል፣ የዴሞክራሲ ተቋማት መገንባት አስገዳጅ ነው ያሉት ደግሞ ዶክተር አየነው ናቸው፡፡ ችግሩን በዘለቄታ ለመፍትት  የመንግስታቱን ግንኙነት የሚመራ ፖሊሲና የህግ ማእቀፍ ለማውጣት ከፌደሬሽን ምክር ቤት ጋር በመተባበር ከተሰራ በኋላ በፌደሬሽን ምክር ቤትና ሚኒስትሮች ምክር ቤት ጸድቆ በተወካዮች ምክርቤት  ለመጽደቅ መመራቱን  አቶ ጣሰው ተናግረዋል፡፡ በህግ ማእቀፉ ረቂቅ  ውይይት ላይ ምሁራን፣ የፌደሬሽን ምክር ቤት መስራቾች ፣ብሄር ብሄረሰቦችና  እንዲሁም  ክልሎች መሳተፋቸውን አስረድተዋል፡፡    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም