ባህርዳር ዩኒቨርሲቲ ለበጋ መስኖ ስንዴ አልሚ አርሶአደሮች በግብዓት አቅርቦትና በቴክኒክ ድጋፍ እያደረገ ነው

67

ባህር ዳር ፤የካቲት 18/2014(ኢዜአ)የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ በ850 ሄክታር መሬት ላይ እየለማ ላለው የበጋ የመስኖ ስንዴ ልማት በግብዓት አቅርቦትና በቴክኒክ ድጋፍ እያደረገ መሆኑ ተገለፀ።

የበጋ መስኖ ስንዴ  ልማቱን ምርታማነት ለማሳደግ ዩኒቨርሲቲው ከ10 ሚሊዮን ብር በላይ ወጭ በማድረግ እየደገፈ መሆኑን በዩኒቨርሲቲው የአስቸኳይ ጊዜ የመስኖ ምርት ልማት አስተባባሪ ዶክተር ተስፋዬ መላክ ለኢዜአ ተናግረዋል።

በዚህም በሰሜን ሜጫ ወረዳ አዲስ ልደት እና አዲስ ዓለም ቀበሌዎች እንዲሁም በባህር ዳር ከተማ ዘንዘልማ የገጠር ቀበሌ በ850 ሄክታር መሬት ላይ እየለማ ላለው የመስኖ ስንዴ በግብዓት አቅርቦትና በቴክኒክ ድጋፍ እያደረገ መሆኑን  ገልጸዋል።

ይህም ምርታማነት ለማሳደግ በልማቱ እየተሳተፉ ለሚገኙ 1ሺህ 300 አርሶ አደሮች 340 ኩንታል ምርጥ ዘርና 1ሺህ 435 ኩንታል ማዳበሪያ እገዛ ማድረጉን አመላክተዋል።

እንዲሁም የግብርና ባለሙያዎች ወደማሳ ወርደው ተከታታይ ሙያዊ ድጋፍ እያደረጉ መሆኑን ዶክተር ተስፋዬ አስታውቀዋል።

የለማውን የስንዴ ሰብል በዘመናዊ መንገድ መሰብሰብ የሚያስችል ኮምባይነር እና ሁለተኛውን ዙር የመስኖ ልማት በተቀላጠፈ መንገድ ማረስ የሚችሉ አራት ትራክተሮችን በማስገባት መካናይዜሽን የማስፋፋት ሥራ እየተከናወነ መሆኑንም አስረድተዋል።

የስንዴ ልማቱ በዘመናዊ መንገድ መከናወኑ ሀገሪቱ በከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ የምታስገባውን ስንዴ በሀገር ውስጥ ለመሸፈን እየተደረገ ያለውን ጥረት ያግዛል" ብለዋል ደከተር ተስፋዬ።

በአማራ ክልል ግብርና ቢሮ የአትክልትና ፍራፍሬ የመስኖ ውሃ አጠቃቀም ዳይሬክተር አቶ ይበልጣል ወንድምነው  እንዳሉት፤ በበጋ መስኖ ስንዴ 38 ሺህ 529 ሄክታር መሬት ለምቷል።

ከዚህ ውስጥ ከ3ሺህ ሄክታር መሬት የሚሆነው በዩኒቨርሲቲዎችና በግብርና ምርምር ድጋፍ የሚለማ መሆኑን ጠቅሰዋል።

ይህም በዩኒቨርሲቲዎቹ ስር ያሉት የግብርና ኮሌጆች ከአካባቢው ማህበረሰብ ጋር በቀጥታ ተገናኝተው አዳዲስ የዘርፉ  አሰራሮችንና ቴክኖሎጂዎችን እንዲመቻቹ  እድል መፍጠሩን ተናግረዋል።

"በዩኒቨርሲቲዎች ድጋፍ በኩታ ገጠም እየለማ ያለውን ስንዴ ለመጪው የመኸር እርሻ ለምርጥ ዘር ግብዓት ጭምር እንዲውል ለማድረግ በቅንጅት እየተሰራ ነው" ብለዋል።

የቢሮው መረጃ እንደሚያሳየው፤ ዘንድሮ በሁሉም የክልሉ አካባቢዎች ያለውን የውሃ አማራጮች በመጠቀም በመስኖ እየለማ ካለው መሬት ከ1 ነጥብ 7 ሚሊዮን ኩንታል በላይ የስንዴ ምርት ይጠበቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም