የህብረት ስራ ማህበራትና ዩኒየኖች ገንቢ ሚና እንዲጫወቱ ለማስቻል ፍኖታ ካርታ እየተዘጋጀ ነው

184

አዳማ፤ የካቲት 18/2014 (ኢዜአ)፡ ከውጭ የሚገቡ የግብርና ምርቶችን በሀገር ውስጥ ለመተካት በሚደረገው ጥረት የህብረት ስራ ማህበራትና ዩኒየኖች ገንቢ ሚና እንዲጫወቱ ለማስቻል ፍኖተ ካርታ እያዘጋጀ መሆኑን የኢትዮጵያ ህብረት ስራ ኮሚሽን አስታወቀ።

ኮሚሽኑ የበጀት ዓመቱ የመጀመሪያዎቹ ስድሰት ወራት   የስራ አፈፃፀምና ቀጣይ አቅጣጫ ላይ በአዳማ ከተማ  የውይይት መድረክ እያካሄደ ነው።

ከውጭ የሚገቡ የግብርና ምርቶችን በሀገር ውስጥ ለመተካት በሚደረገው ጥረት ውስጥ የህብረት ስራ ማህበራትና ዩኒየኖች ገንቢ ሚና እየተጫወቱ መሆናቸውን የኢትዮጵያ የህብረት ስራ ኮሚሽን ኮሚሽነር ወይዘሮ ፍሬህይወት ሽባባው  ገልጸዋል።

የበጋ የስንዴ መስኖ ልማት ላይ ዩኒየኖችና መሰረታዊ ማህበራት በንቃት እየተሳተፉ መሆኑን ጠቅሰው፤ በቀጣይም አትክልትና ፍራፍሬን ጨምሮ በሁሉም የሰብል ዓይነቶች እንደሚቀጥል ጠቁመዋል።

ዩኒየኖችና ማህበራት የአሰራርና አመራር ችግር፣የሰው ሃይል እጥረት ፣የአቅርቦት ፣የፋይናንስ ውስንነትና የአቅም ችግር እንደሚታይባቸው የጠቆሙት  ኮሚሽነሯ፤ እየተዘጋጀ ያለው ፍኖተ ካርታ በአቅም ግንባታ፣አሰራርና የአመራር ስርዓታቸውን ማዘመን ላይ ትኩረት  ማድረጉን አስረድተዋል።

ፍኖተ ካርታው በሀገር ውስጥና በውጭ ገበያ ያላቸው የመወዳደር አቅም፣በገበያ ማረጋጋት፣በግብርና ግብዓትና ለአርሶ አደሩ የመካናይዜሽን አገልግሎት ተደራሽ በማድረግ ረገድ ያላቸውን አቅም እንደሚያሳድግ አመልክተዋል።

ባለፉት ስድስት ወራት የግብርና ምርቶች የዋጋ ንረትና ገበያ ለማረጋጋት ማህበራት አዲስ አበባ፣ኦሮሚያ፣ድሬ ደዋና ሀዋሳን  የእሑድ ገበያ በመክፈት ዩኒየኖች ከአምራቹ አርሶ አደር የተለያዩ የግብርና ምርቶችን በመሰብሰብ ለሸማቹ እያቀረቡ መሆኑን ተናግረዋል።

በዘላቂነት አርሶ አደሩ ምርታማነቱን ማሳደግ እንዲችልና የሚታየውን የምርት እጥረት ችግር ለማቃለል ፍ አቅጣጫ ተቀምጦ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

በአሁኑ ወቅት በበጋ ስንዴ መስኖ ልማት በተለይም  በቆላ ስንዴ የዘር ብዜት ላይ መሰረታዊ ማህበራት እየሰሩ መሆኑን የገለጹት ደግሞ  በኮሚሽኑ የህብረት ስራ ግብይት ዳይሬክተር ወይዘሮ ይርጋለም እንየው ናቸው።

ከዋናው የመኽር ስብል ምርት አሰባሰብ በተጨማሪ በመስኖ እየለማ ያለው ስንዴ በወቅቱ እንዲሰበሰብ  ለአጨዳ አገልግሎት የሚውል ኮምፓይነር በማህበራት በኩል ለአርሶ አደሩ እየቀረበ መሆኑን ተናግረዋል።

 አርሶ አደሩ በተመጣጣኝ ዋጋ አግልግሎቱን እንዲያገኝና ምርቱንም በተሻላ ዋጋ ለዩኒየኖች እንዲሸጥ  የገበያ ትስስር መፈጠሩንም አመልክተዋል።

አርሶ አደሩ በሰራው ልክ ተጠቃሚ እንዲሆን ያለባት  የፋይናንስ አቅም ውስንነትና የካፒታል ችግር ለማቃለል  በልዩ ሁኔታ እየሰራን ነው ብለዋል።

ዩኒየኖች በጦርነቱ ምክንያት አኩሪ አተር፣እጣንና ሙጫ፣ሰልጥና ሌሎች ምርቶች ለገበያ ማቅረብ እንዳልቻሉ የጠቀሱት ዳይሬክተሯ፤  ይሄም በዘርፉ በግማሽ ዓመቱ የውጭ ግብይት ዝቅተኛ እንዲሆን ማድረጉን ተናግረዋል።

የተጎዱትን ዩኒየኖችና የህብረት ስራ ማህበራት መልሶ ለማደራጀት እየተሰራ መሆኑንም ጠቁመዋል። 

በመድረኩ  ከክልሎችና ከተማ አስተዳድሮች የተወጣጡ  የህብረት ስራ ሴክተሮች እየተሳተፉ መሆኑን ኢዜአ ከአዳማ ዘግቧል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም