የአገር ውስጥ የቱሪስት መስህቦችን የመጎብኘት ባህላችን ሊጎለብት ይገባል

84

የካቲት 18/2014/ኢዜአ/ የአገር ውስጥ  የቱሪስት መስህቦችን የመጎብኘት ባህላችን ሊጎለብት ይገባል ሲሉ ኢዜአ ያነጋገራቸው የአገር ውስጥ ጎብኚዎች ገለጹ፡፡

የአገር ውስጥ ቱሪዝም በዋናነት ዜጎች ከሚኖሩባቸው አካባቢዎች ለመዝናናት፣ ለስብሰባ፣ ለመስክ ሥራ፣ ለሃይማኖታዊ ጉዞ እና ለህክምና በአገር ውስጥ የሚያደርጉት እንቅስቃሴና ጉብኝት ሲሆን፤ይህም ከኢኮኖሚያዊ ፋይዳው ባሻገር በሕዝቦች መካከል አብሮነትን ያጠናክራል፡፡

ኢትዮጵያ በርካታ ተፈጥሯዊና ባህላዊ የቱሪስት መዳረሻ ሥፍራዎች ቢኖራትም የአገር ውስጥ ቱሪዝም በሚፈለገው ልክ አልጎለበትም፡፡

ኢዜአ በአንድነት ፓርክ በመገኘት ያነጋገራቸው ጎብኚዎች እንደሚሉት፤ ያሉንን የቱሪስት መስህቦች የመጎብኘት ባህላችን ሊጎለብት ይገባል ፡፡

አቶ ጥላሁን አባዝናብ ኢትዮጵያ ለቱሪዝም ልማት ምቹ አገር መሆኗን ገልጸው፤ በተለይ የአገር ውስጥ ቱሪዝም እንዲጎለብት መሰራት እንዳለበት ተናግረዋል፡፡

አገራችንን የመጎብኘት ባህል ሊዳብር ይገባል ሲሉም ነው የተናገሩት፡፡

ወይዘሮ ህይወት ወንድሙ፤ እንደ አንድነት ፓርክ ያሉ የቱሪስት መዳረሻዎችን በማልማት የአገር ውስጥ ቱሪዝምን ማጎልበት እንደሚቻል ተናግረዋል፡፡

የተመለከትናቸው መልካም ነገሮችን ለሌሎች በማሳወቅ የጉብኝት ባህል እንዲዳብር መሥራት እንደሚጠበቅም  አስተያየት ሰጪዎቹ አሳስበዋል፡፡

የአንድነት ፓርክ ምክትል ሥራ አስኪያጅ አቶ ብርሀኑ ንጉሴ በበኩላቸው፤ በየአካባቢው ያሉ የቱሪዝም መዳረሻዎችን ኀብረተሰብን አስተባብሮ በማልማት የአገር ውስጥ ጎብኚዎችን ቁጥር ማሳደግ እንደሚቻል ተናግረዋል፡፡

በዚህ ረገድ አንድነት ፓርክ ተጠቃሽ መሆኑን ጠቅሰው፤ ፓርኩን እስካሁን ባለው ሂደት ከግማሽ ሚሊዮን በላይ ዜጎች እንደጎበኙት ተናግረዋል፡፡

በቱሪዝም ሚኒስቴር የአገር ውስጥ ቱሪዝምን ለማሳደግ የተለያዩ ተግባራትን እያከናወነ መሆኑን የተናገሩት ደግሞ በሚኒስቴሩ የአገር ውስጥ ቱሪዝም ማስፋፊያ ዳይሬክተር ሙሉነህ ማቴዎስ ናቸው፡፡

በተጨማሪ ሚኒስቴሩ በአሸባሪው ህወሓት ወረራ ምክንያት ጉዳት በደረሰባቸው አካባቢዎች ያለውን የቱሪዝም እንቅስቃሴ ለማነቃቃት ሁነቶችን ከማዘጋጀት ጀምሮ ከሁሉም ባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እየሰራ መሆኑን አንስተዋል፡፡

በትምህርት ቤቶች ያሉ የአገርህን እወቅ ክበባትን እንቅስቃሴ በማገዝ ዘርፉን ለማነቃቃት እየተሰራ መሆኑንም እንዲሁ፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም