ምክክሩ የኢትዮጵያውያን አንድነት የሚጠናከርበትን መሰረት ይጥላል-ነዋሪዎች

69

ባህር ዳር የካቲት 18/2014 (ኢዜአ) ሊካሄድ የታሰበው አገራዊ የምክክር መድረክ "ኢትዮጵያዊያን የሚያራርቁንን ጉዳዮች በውይይት በመፍታት አንድነታችንን የምናጠናክርበት መሠረት ይጥላል" ሲሉ የባህር ዳር ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ።

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በዋና ዋና አገራዊ ጉዳዮች ላይ ብሔራዊ መግባባት ለመፍጠር ያስችላል የተባለውን የኢትዮጵያ አገራዊ የምክክር ኮሚሽን ማቋቋሚያ ዓዋጅ ቁጥር 1265 /2014 በዚህ ሳምንት አጽድቋል።

በዚህም መሠረት ኮሚሽኑን የሚመሩት 11 ኮሚሽነሮች ለመለየት ከኅብረተሰቡ ከ600 በላይ ሰዎች ተጠቁመዋል።

ከተጠቆሙት ግለሰቦች መካከል 42ቱ ዓዋጁን መሠረት ተደርጎ የተለዩ ሲሆን፤ ኅብረተሰቡም አስተያየት እንዲሰጥባቸው ተደርጓል።

በመሆኑም አገራዊ ምክክሩን ለመምራት 11ድ ኮሚሽነሮች ለምክር ቤቱ ቀርበው ሹመታቸው ጸድቋል።

ይህንኑ ተከትሎ ኢዜአ ያነጋገራቸው አንዳንድ  የባህር ዳር ከተማ ነዋሪዎች በሰጡት አስተያየት ሊካሄድ የታሰበው ሀገራዊ የምክክር መድረክ እንደ አገር የገጠሙንን ችግሮች በውይይት በመፍታት አንድነታችንን ለማጠናከር መሠረት ይጥላል የሚል እምነት እንዳላቸው ገልጸዋል።

ከነዋሪዎቹ መካከል አቶ ታዘባቸው ጣሴ አገራዊ ችግሮቻችንን ለመፍታት በሐቅ ላይ የተመሰረተ፣ ግልፅና ትክክለኛ አገራዊ ውይይት ማካሄድ አስፈላጊ መሆኑን ተናግረዋል።

አገራዊ ምክክሩ እንደ ሀገርም ሆነ እንደ ክልል የሚስተዋሉ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና ስነ-ልቡናዊ ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት የጎላ ፋይዳ እንዳለው አመልክተዋል።  

"ፖለቲካዊ ፋይዳውን ብቻ ወስደን ስንመለከት ከማንነትና ከወሰን ጥያቄዎች ጋር በተያያዘ በየቦታው የሚታዩት ግጭቶችና አለመግባባቶች ዘላቂ እልባት ያገኛሉ ብየ አምናለሁ" ብለዋል።

ምክክሩ በሕገ መንግሥቱ ውስጥ የተቀመጡና ልዩነት የሚፈጥሩ አንዳንድ አንቀፆችን ለማስተካከል እንደሚያስችልና የዜጎች ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች እንደሚከበሩ መሰረት የሚጣልበት እንደሚሆን እምነታቸውን ገልጸዋል።

እንዲሁም የህዝብ ለህዝብ ትስስር ለማጠናከርና ማንኛውም ኢትዮጵያዊ በየትኛውም ቦታ ከስጋት ነፃ ሆኖ ተንቀሳቅሶ በመስራት ራሱንና ሀገሩን መጥቀም የሚችልበትን ህገ መንግስታዊ መብት ለማስከበር ያስችላል የሚል እምነት እንዳላቸው አመልክተዋል ።

ሌላኛው የከተማው ነዋሪ አቶ ሰውነት ተገኘ በበኩላቸው አገራዊ ምክክሩ የተለያየ አስተሳሰብ ያላቸውን ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች በአገራዊ ጉዳዮች ላይ ወደ መግባባት ሊያመጣ እንደሚችል እምነታቸውን ገልጸዋል።

በሕዝብ መካከል ያለውን አንድነት ለማጠናከርና ጠንካራ አገር ለመፍጠር የሚደረገውን ጥረት ለማሳደግ እንደሚያስችል ተናግረዋል።

አገራዊ ምክክሩ ከታችኛው የህብረተሰብ ክፍል ቢጀመር መልካም መሆኑን ገልጸው ዓለም አቀፍ ግንዛቤ ያላቸውና ታሪክን የሚያውቁ ሰዎች ቢሳተፉበት ደግሞ በአገሪቱ ዘላቂ ሰላም ለማስፈን ያስችላል ብለው እንደሚያምኑ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም