በጎንደር ከተማ ቦምብ ፈንድቶ የሁለት ሰዎች ህይወት አለፈ በሰባቱ ላይ ደግሞ የአካል ጉዳት ደረሰ - ኢዜአ አማርኛ
በጎንደር ከተማ ቦምብ ፈንድቶ የሁለት ሰዎች ህይወት አለፈ በሰባቱ ላይ ደግሞ የአካል ጉዳት ደረሰ
ጎንደር፣ የካቲት 18/2014 ( ኢዜአ) በጎንደር አዘዞ ክፍለ ከተማ አንድ የጭነት አይሱዚ መኪና ሲፈተሸ በድበቅ ጭኖት የነበረው ቦምብ ፈንድቶ ሁለት ሰዎች ሲሞቱ በሰባት ሰዎች ላይ ደግሞ የአካል ጉዳት መድረሱን የጎንደር ከተማ አስተዳደር ፖሊስ መምሪያ አስታወቀ፡፡
የመምሪያው የሚዲያና ኮሙዩኒክሽን ክፍል ኃላፊ ዋና ኢንስፔክተር እየሩስዓለም አስማረ ለኢዜአ እንደገለጹት አደጋው የደረሰው ዛሬ ከቀኑ 8 ሰዓት ተኩል ላይ ነው።
የሰሌዳ ቁጥሩ ኮድ3 -32877 አዲስ አበባ የሆነው አይሱዚ የጭነት ተሸከርካሪ ከመተማ ተነስቶ ወደ ጎንደር በመግባት ላይ እያለ በአዞዞ ክፍለ ከተማ በሚገኘው ፖሊስ ጣቢያ ጭነቱ በሚፈተሸበት ወቅት የቦምብ ፍንዳታው መከሰቱን ገልጸዋል።
በፍንዳታው ተሸከርካሪውን በመፈተሸ ላይ የነበሩ ሁለት የፖሊስ አባላት ሲሞቱ ሌሎች የፖሊስ አባላትን ጨምሮ በአካባቢው የነበሩ ሰባት ሰዎች ላይ ደግሞ ከባድና ቀላል የአካል ጉዳት መድረሱን ተናግረዋል።
በአደጋው ጉዳት የደረሰባቸው የፀጥታ አባላትና ነዋሪዎች በጎንደር ዩኒቨርስቲ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የህክምና እርዳታ እየተደረገላቸው መሆኑንም አስታውቀዋል።
የመኪናው አሽከርካሪ ለጊዜው መሰወሩን የጠቆሙት፤ ኢንስፔክተር እየሩስዓለም ፖሊስ የአደጋውን መንስኤና ድርጊቱን በማጣራት ላይ እንደሚገኝ አስታውቀዋል።
አሽከርካሪዎች በተሰጣቸው ኃላፊነት ልክ በህዝብና በሀገር ላይ ጉዳት ከሚያደርሱ የወንጀል ድርጊቶች ተቆጥበው ኃላፊነታቸውን መወጣት እንዳለባቸውም አስገንዝበዋል።