በኢትዮጵያ የኢንዱስትሪ ምህንድስና ፍላጎት እየጨመረ መጥቷል

133
አዲስ አበባ ነሃሴ 26/2010 በኢትዮጵያ የኢንዱስትሪ ምህንድስና ፍላጎት እየጨመረ መምጣቱ ተጠቆመ፡፡ የኢትዮጵያ ኢንዱስትሪያል ማህበር ሁለተኛ  አመታዊ ጠቅላላ ጉባኤውን ዛሬ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አካሂዷል፡፡ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት የሜካኒክልና ኢንዱስትሪያል ኢንጂነሪንግ ትምህርት ክፍል መምህርና ተመራማሪ ፕሮፌሰር ዳንኤል ቅጣው ''የኢንዱስትሪያል ምህንድስና ፍላጎት እየጨመረ መጥቷል'' ብለዋል። ለፍላጎቱ መጨመር ዋነኛ ምክንያቱ አገሪቱ ከግብርና መር ወደ ኢንዱስትሪ መር ኢኮኖሚ ሽግግር ውስጥ መግባቷ እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡ እንዲህም በኢንዱስትሪያል ምህንድስና ተማራቂዎች ዘርፈ ብዙ ሌሎች የትምህርት ክፍሎች ትምህርቶችን መውሰዳቸው ተፈላጊነታቸውን እያሳደገው መምጣቱን ነው ፕሮፌሰር ዳንኤል የተናገሩት፡፡ ይሁን እንጂ የዘርፉን ባለሙያዎች በትክክለኛው የስራ መስክ ከማሰማራት ጋር በተያያዘ ችግሮች መኖራቸውን ጠቁመዋል፡፡ በተለይም ለኢንዱስትሪው የሚሆኑ ቴክኖሎጂዎችን ከመምረጥ፣ ስምምነት ከማድረግ፣ ከማጓጓዝ፣ ጥገና ከመስጠትና ባለሙያዎችን በማሰልጠን በኩል ክፍተቶች መኖራቸውን አመላክተዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት ደግሞ አገሪቱ የተለያዩ የኢንዱስትሪ ፓርኮችን እየገነባች በመሆኑ፤ የዘርፉን ምሁራን በስፋት በተገቢው ቦታ በመመደብና በማሰራት ውጤታማ ስራ መስራት እንደሚገባም ፕሮፌሰር ዳንኤል ተናግረዋል፡፡ ኢንዱስትሪው በጥራቱና በአገልግሎቱ ደረጃውን የጠበቀ ምርትና አገልግሎት እንዲሰጥ የኢንዱስትሪ ምህንድስና ባለሙያዎችና መንግስት ተቀራርበው መስራት እንደሚኖርባቸውም ገልጸዋል፡፡ በኢትዮጵያ ኢንዱስትሪያል መሃንዲሶች ማህበር የቦርድ አባልና በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት የሜካኒካልና ኢንደስትሪያል ኢንጂነሪንግ ትምህርት ክፍል ባልደረባ ዶክተር አምሃ ሙሉጌታ አገሪቱ የምትፈልገውን በቁ የኢንዱስትሪ  ምህንድስና ባለሙያ ፍላጎት ለማሳካት እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ ለዚህም በአገር አቀፍ ደረጃ የኢንዱስትሪ መሀንዲሶች ማህበር ከማቋቋም ጀምሮ፤ እውቀትና ክህሎትን የሚያዳብሩ ስልጠናዎችን መስጠት እንዲቻል ጥረት እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ በዘርፉ ተመርቀው የሚወጡ ባለሙያዎችን ከንድፈ ሀሳብ ስልጠና ጀምሮ በተግባር የታገዘ በማድረግ ጊዜው የሚጠይቀውን ባለሙያ ለማፍራት ጥረት በመደረግ ላይ መሆኑንም ዶክተር አምሃ ገልጸዋል፡፡ የዘርፉ ባለሙያዎች ማህበሩ በሰጣቸው የንድፈ ሀሳብና የተግባር ስልጠናዎች የእውቅና ፈቃድ በመስጠት ተወዳዳሪነታቸውን ለማሳደግ እንደሚሰራም ተጠቁሟል፡፡ ማህበሩ ውጤታማ የኢንዱስትሪ ምህንድስና ባለሙያዎችን ለማፍራት በሚደረገው ጥረት መንግስት ባለሙያዎችን የሚያበረታታና የሚደግፍ የፖሊሲ ማዕቀፎችን ሊያዘጋጅ እንደሚገባም ጠቁመዋል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም