ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከእስር ቤት ስለተፈቱ ግለሰቦች ለምክር ቤቱ የሰጡት ምላሽ ግልጽነትን ፈጥሯል-የባህር ዳር ነዋሪዎች

71

ባህር ዳር የካቲት 17/2014(ኢዜአ) የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ደክተር ዐቢይ አሕመድ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ከእስር ቤት ስለተፈቱ ግለሰቦችና በሌሎችም ወቅታዊ ጉዳዮች ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች የሰጡት ምላሽ በሕዝቡ ዘንድ የነበሩ ብዥታዎችን እንዳጠራ አድርጓል ሲሉ የባህር ዳር ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ከምክር ቤቱ አባላት የተነሱላቸውን ጥያቄዎችና የሰጡትን ምላሽ በተመለከተ ኢዜአ  አንዳንድ የከተማው ነዋሪዎችን አነጋግሯል።

ከከተማው ነዋሪዎች መካከል አቶ ላንተይደሩ ተስፋዬ እንደገለጹት የአሸባሪው ህወሓት ነባር አመራር አባላት በታኅሣሥ 2014 ዓ.ም መጨረሻ ከእስር መፈታታቸው ከፍተኛ ቅሬታ ፈጥሮ ነበር።

እሳቸውን ጨምሮ በርካቶች የአሸባሪው ቡድን ነባር አመራሮች በመፈታታቸው የተደበላለቀ ስሜት ፈጥሮባቸው እንደነበር ገልጸዋል።

ከእስር የተፈቱት አመራሮች አገርን በከፍተኛ ሁኔታ የበደሉና ለውድመት የዳረጉ፣ ኢትዮጵያዊያንን ለማለያየት በጥላቻ ስሜት በመስራታቸውና ኢትዮጵያን ለማፍረስ ስምሪት መስጠታቸው ለቅሬታው ምክንያት መሆኑን አመልክተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ሰሞኑን ለምክር ቤቱ ግለሰቦቹ የተፈቱበት ሁኔታ የተገኘውን ድል ለማፅናትና ዘላቂ ሰላም ለማምጣት መሆኑን በማብራራታቸው በግለሰቦቹ አፈታት ላይ የነበራቸውን ስሜት እንደቀየረውና ትክክልኛና አሳማኝ ሆኖ እንዳገኙት አቶ ላንተይደሩ ተናግረዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ አገራዊ ምክክርን አስመልክቶ የሰጡት ምላሽ በሃሳብ ደረጃ ትክክለኛ፣የሚያስማማና ሳይንሳዊ ነው" ያሉት ደግሞ አቶ ሙላት መኳንንት የተባሉ ሌላኛው የከተማው ነዋሪ ናቸው።

''ከአሸባሪው ህወሓት ጋር ድርድር እየተደረገ ነው'' በሚል የሚናፈሰውን ሀሰተኛ ወሬ ግልፅ ማድረጋቸው ተገቢና ወቅታዊ እንደሆነ አስረድተዋል።

''መደራደር ማለት ማፍረስ ማለት አይደለም'' ያሉት አስተያየት ሰጪው ''ነገር ግን ሁኔታዎችን በስሜት ሳይሆን በስሌት መነጋገርና መወያየት መፍትሄ አለው'' ሲሉም ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም