ከደቡብ ክልል ለህዳሴ ግድብ ከ22 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ ተሰባስበ

66

ሶዶ፤የካቲት 17/2014 (ኢዜአ) ከደቡብ ክልል ባለፉት ስድስት ወራት ለህዳሴ ግድብ ግንባታ ከ22 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ መሰብሰቡን የክልሉ የህዳሴ ግድብ የህዝብ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ምክር ቤት ጽህፈት ቤት አስታወቀ።

የደቡብ ክልል የህዳሴ ግድብ የህዝብ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ምክር ቤት የበጀት ዓመቱ የስድስት ወራት አፈጻጸም ግምገማ መድረክ በወላይታ ሶዶ ከተማ እያካሄደ ነው።

የጽህፈት ቤቱ ሃላፊ አቶ ሚልኪያስ እስራኤል በመድረኩ ላይ እንደገለጹት ባለፉት ስድስት ወራት ለህዳሴ ግድብ ክልሉ  114 ሚሊዮን ብር ለማሰባሰብ አቅዶ  ሲሰራ ቆይቷል።

በወራቶቹ በነበረው አፈጻጸም ከቦንድ ግዥና ከተለያዩ ድጋፎች ከ22 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ መሰብሰቡን ተናግረዋል።

በህወሓት አሸባሪ ቡድን ምክንያት በሀገር ላይ የተቃጣው ጦርነትና ሌሎች የጸጥታ ችግሮች የእቅድ አፈጻጸሙ ዝቅተኛ እንዲሆን ማድረጉን አመልክተዋል።

በአፈጻጸም ግምገማ መድረኩ ባለፉት ስድስት ወራት የነበሩ ጠንካራና ደካማ ጎኖች ተለይተው በበጀት ዓመቱ የተያዘውን ግብ ለማሳካት እንደሚሰራ አመላክተዋል።

ኢትዮጵያዊያን ትልልቅ ፕሮጀክትን በራሳቸው አቅም መፈጸም እንደሚችሉ የታላቁ የህዳሴ ግድብ ያረጋገጠ ፕሮጀክት መሆኑን የገለጹት ሃላፊው ግድቡ ኃይል ማመንጨት መጀመሩ ትልቅ ስኬት መሆኑን ጠቅሰዋል።

"ኢትዮጵያዊያን አንድነታችንን ካጠናከርን በቀጣይ ግንባታውን የማጠናቀቅ ስራዎች ከባድ አይሆኑም" ሲሉ አመላክተዋል።

የክልሉ ህዝብ የፕሮጀክቱ ግንባታ መሰረተ ድንጋይ ከተቀመጠለት ጊዜ አንስቶ በቦንድ ግዢና በተለያዩ ድጋፎች ከ1 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር በላይ ድጋፍ ሲያደርግ መቆየቱን ጠቁመዋል።

በመድረኩ ላይ በክልሉ የሁሉም የዞኖች፣ ልዩ ወረዳዎች የባለድርሻ አካላት እየተሳተፉ መሆኑ ተመላክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም