የኑሮ ውድነትን ለማርገብ እየተወሰደ ያለው የመፍትሄ እርምጃ የሚደገፍ ነው-የሐዋሳና የይርጋለም ነዋሪዎች

54

ሐዋሳ፤ የካቲት 17/2014 (ኢዜአ) እየተባባሰ የመጣውን የኑሮ ውድነት ለማርገብ መንግሥት እየወሰደ ያለው የመፍትሄ እርምጃ የሚደገፍ ነው ሲሉ አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ የሐዋሳና የይርጋለም ከተማ ነዋሪዎች ተናገሩ።
በኑሮ ውድነት እና በሌሎች ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ  ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ለተነሱላቸው ጥያቄዎች የሰጡት ማብራሪያና ምላሽ ተገቢና የሚደገፍ መሆኑን ነዋሪዎቹ ጠቁመዋል።

ከአስተያየት ሰጪዎቹ መካከል የሀዋሳ ከተማ ነዋሪ አቶ ታዱ ተክሉ የኑሮ ውድነት ቀደም ሲልም በተከታታይ ዓመታት የነበረና በዚያው መቀጠሉን ጠቅሰው፤ በአሁኑ ወቅትም በርካታ የግንባታ እቃዎች ቀድሞ ከነበራቸው ዋጋ አኳያ ጭማሪ አሳይተዋል ብለዋል።

"መሰረታዊ የፍጆታ እቃዎች ላይም የዋጋ ግሽበት በስፋት ይታያል" ያሉት አቶ ታዱ በተለይ በጦርነት ውስጥ የቆየች ሀገር ቀርቶ ጦርነት የሌለባቸውም ሀገራት በኑሮ ውድነት ተጠቂ መሆናቸውን ተናግረዋል።

የኑሮ ውድነቱን ሆን ብለው እንዲባባስ የሚያደርጉ አካላት መኖራቸውን የጠቆሙት አቶ ታዱ መንግሥት ከህብረተሰቡ ጋር በመቀናጀት ሴራውን ሊያከሽፈውና ሊያስተካክለው እንደሚችል ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።

በሀገሪቱ ያጋጠመውን  የኑሮ ውድነትን ለመግታት በመንግሥት እየተወሰዱ ካሉ የመፍትሄ እርምጃዎች መካከል አንዱና ዋነኛው የበጋ ስንዴ ልማትና ኩታ ገጠም አስተራረስ ዘዴ መሆኑን ጠቁመው፤ ይህም ሀገሪቱን በምግብ ሰብል ራስን ለማስቻል ለሚደረገው ጥረት ወሳኝ በመሆኑ በየደረጃው ሊስፋፋ እንደሚገባ ተናግረዋል።

በዚህ ረገድ እየተካሄዱ ያሉ የልማት ስራዎች ሀገሪቱን ወደ ፊት ሊለውጧትና ለሌሎችም ሀገራት ልማዷን ለመካፈል የሚያስችላት ስለሆነ በየደረጃው የሚገኘው አርሶ አደርና ህብረተሰቡ ለልማቱ ስኬታማነት ሊረባረብ እንደሚገባ አስታውቀዋል።

ለኑሮ ውድነት መባባስ መንስዔ እየሆነ የመጣው ህገ ወጥ የነዳጅ ንግድ እንዲገታ መንግሥት ጠንካራ ቁጥጥርና ጠበቅ ያለ እርምጃ እንዲወስድም ጠይቀዋል።

በሀዋሳ የምስራቅ ክፍለ ከተማ ነዋሪ አቶ ሰለሞን አንጀሎ በበኩላቸው በአገሪቱ ጤናማ የመግዛትና የመሸጥ ውድድር ሥርዓት ባለመዘርጋቱ፣ በየደረጃው ከተንሰራፋው የመልካም አስተዳደርና ሙስና ችግር ጋር ተዳምሮ የኑሮ ውድነቱን  እንዳባባሰው ተናግረዋል።

ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሻቀበ ያለው የዋጋ ንረት በተለይ እሳቸውን ጨምሮ በዝቅተኛ ገቢ የሚተዳደሩ የሀገሪቱን ዜጎች ብርቱ ፈተና ውስጥ እንደከተታቸው ተናግረዋል።

ህብረተሰቡ ያልተገባ የዋጋ ጭማሪ በማድረግ ህዝብን የሚያማርሩና ህዝብም በመንግስት ላይ እንዲነሳሳ ግፊት የሚያደርጉ አካላትን  በማጋለጥ ከመንግስት ጋር ሊተባበር እንደሚገባ አስረድተዋል።

ሌላው የይርጋለም ከተማ ነዋሪ አቶ ተስፋዬ አረጋ  በሰጡት አስተያየት "የማኅበረሰቡ የዕለት ተዕለት መሠረታዊ ፍላጎት የሆኑት ሸቀጣ ሸቀጦች፣ ቁሳቁሶች፣ የምግብ ነክ ዋጋ ጭማሪዎች የነዋሪውን ህልውና እየተፈታተኑት ይገኛሉ" ብለዋል።

የኑሮ ውድነቱ ህዝቡን ያስጨነቀው ጉዳይ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተረድተው  በቀጣይ መወሰድ ስላለባቸው የመፍትሄ እርምጃዎች በማስመልክት የሰጡት ገለፃና ማብራሪያ ተስፋ የሚሰጥ መሆኑን አውሰተዋል።

"ህገ ወጥነትን በዘላቂነት ለመከላከል ከህዝብ ጋር ተባብሮ ብዙ ስራ መስራት ይቻላል" ያሉት አቶ ተስፋዬ በተለይ በአቋራጭ ለመበልጸግ በሚሯሯጡ አካላት ላይ አስተማሪ እርምጃ በመውሰድ መጪውን ትውልድ መታደግ እንደሚያስፈልግ አስታውቀዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከትናንት በስትያ በነበረው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሶስተኛ አስቸኳይ ስብሰባ በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ከምክር ቤት አባላት ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ምላሽ መስጠታቸው ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም