የአንበጣ መንጋ በአፍሪካ ቀንድ አገራት አስጊነቱ እየቀነሰ መጥቷል

90

አዲስ አባባ የካቲት 17/2014 ኢዜአ/ በአፍሪካ ቀንድ አገራት የአንበጣ መንጋ አስጊነቱ እየቀነሰ መምጣቱን የምሥራቅ አፍሪካ የበረሃ አንበጣ መከላከል ድርጅት አስታወቀ።
ኢትዮጵያና ኬንያን ጨምሮ በቀጣናው አገራት ዝናብ አለመኖሩ ለአንበጣ መንጋው መቀነስ ምክንያት መሆኑን ጠቅሷል፡፡

የድርጅቱ የመረጃ እና ትንበያ ከፍተኛ ባለሙያ አቶ ፈለገ ኤልያስ፤ ቀደም ባሉት ዓመታት በአፍሪካ ቀንድ የአንበጣ መንጋ በእፅዋትና ሰብሎች ላይ ከፍተኛ ጉዳት ማድረሱን አስታውሰዋል።

የአንበጣ መንጋው በኢትዮጵያ፣ ጅቡቲ፣ ኬንያ፣ ኡጋንዳ፣ ታንዛኒያ እና ደቡብ ሱዳን ከፍተኛ ጉዳት ማድረሱንም ጠቅሰዋል።

በጥር ወር በፑንትላንድ ቦሳሶ እና ገረዌ አካባቢዎች ላይ አነስተኛ መጠን ያለው የአንበጣ መንጋ ተከስቶ የነበረ ቢሆንም ካለፈው አንድ ዓመት ጀምሮ ስጋቱ እየቀነሰ መጥቷል ብለዋል።

በኢትዮጵያም ወርዴር፣ ቆራሄ እና ሳሄል በተባሉ አካባቢዎች ላይ መጠነኛ የአንበጣ መንጋ ታይቶ የነበረ ቢሆንም በሌሎች አካባቢዎች ስጋት የለም ነው ያሉት።

በቀጣናው የጣለው የዝናብ መጠን ዝቅተኛ በመሆኑ እንዲሁም በአካባቢው የተከሰተው ድርቅ የአንበጣ መንጋው እንዳይፈለፈል እና እንዲቀንስ ምክንያት ሆኗል ብለዋል።

በዚህም ዝናብ አምጪ ሁኔታዎች ካለመስተዋላቸው ጋር ተያይዞ የአንበጣ መንጋው እርጥበታማ አፈር ማግኘት ካልቻለ ሁኔታዎች በዚሁ ሊቀጥሉ እንደሚችሉም ተናግረዋል፡፡

የአንበጣ መንጋ ዘንድሮ በአህጉሪቱ በተለያዩ አካባቢዎች ላይ ከተከሰተው ድርቅ በተጨማሪ ሌላ ስጋት እንዳይሆን አስቀድሞ የመከላከል ስራዎች እየተሰሩ እንዳሉም ገልጸዋል።

የአንበጣ መንጋውን አስቀድሞ ለመከላከል እና ከተከሰተም በቶሎ ለመቆጣጠር እንዲያስችል የመሰረተ ልማቶች ግንባታ እየተከናወነ ሲሆን በኢትዮጵያም በተለያዩ አካባቢዎች ላይ ተዛማጅ ተባዮችን መከላከያ ማዕከላት እየተቋቋሙ እንደሆነም ጠቁመዋል።  

የበረሃ አንበጣ በአብዛኛው የሚከሰተው በረሃማ በሆኑ አካባቢዎች በመሆኑ በድሮን ጭምር አሰሳ ለማድረግ ዝግጅት እየተደረገ ነው ብለዋል።

በዚህም አገራት የአንበጣ መንጋውን ለመቆጣጠር እየተደረገ ያለውን ጥረት ማጠናከር ይኖርባቸዋል ብለዋል።

በ2011 ዓ.ም የበረሃ አንበጣ መንጋ በኢትዮጵያ፣ ሶማሊያና ኬንያ ከፍተኛ ጉዳት ማድረሱ ይታወሳል።

በኢትዮጵና በሶማሊያ በ25 ዓመት ውስጥ አስከፊ ሆኖ የተመዘገበ ሲሆን በኬንያ የታየው ደግሞ ከ70 ዓመታት በኋላ የተከሰተ አስከፊው የአንበጣ መንጋ ሆኖ ተመዝግቧል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም