ለምንድን ነው?

162

(በመንበረ ገበየሁ ሐዋሳ ኢዜአ)

ዕለቱ ቅዳሜ የካቲት 12 ቀን 2014 ዓ.ም ነው። በሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ ግብርና ኮሌጅ የዩኒቨርሲቲ ምሩቃንን ጨምሮ በርካታ ወጣቶች የተሳተፉበት ኹነት ተዘጋጅቷል።የኹነቱ አዘጋጅ ደግሞ የአትዮጵያ ወጣቶችና ትምህርት ድጋፍ አገልግሎት /YessEthiopia/  የተሰኘ የበጎ አድራጎት ማህበር ነው።

በኮሌጁ የስነ ምግብ ሳይንስ ቴክኖሎጂ መምህሩ ረዳት ፕሮፌሰር ፈቃዱ ረታ የማህበሩ መስራች ናቸው። ኹነቱ ታዋቂ ሰዎች ልምዳቸውን ለወጣቶች ያካፈሉበት፤ በንግግራቻው ታዳሚውን እያዋዙ አስደምምው ያነቃቁበት ነው።

ኑሯቸውን በአዲስ አበባ ያደረጉት የጠብታ አምቡላንስ ባለቤትና መስራች አቶ ክብረት አበበ  የመጀመሪያው ተናጋሪ ናቸው። ጠብታ አምቡላንስ በድንገተኛ ሕክምና ላይ የሚሰራ ማህበራዊ አገልግሎት የሚሰጥ ተቋም ነው። አቶ ክብረት እንደሚሉት ''ለምን የጥያቄዎች ማዕከል ነው፤ ለምንን የሚመልሱ ሰዎች ውስጣቸው ብዙ ኃይል አለ።'' በመድረክ ለሚያቀርቧቸው ሀሳቦች ርዕስ የመስጠት ልምድ አላቸው። የዕለቱን የንግግራቸውንም ለምንድን ነው? የሚል ርዕስ ሰጥተውታል።

አቶ ክብረት የለምንድን ነው? ፅንሰ-ሃሳብ እንዲህ ሲሉ ነው በአንክሮ ለሚከታተሏቸው፤ በጥሞና ለሚያዳምጧቸው አብራርተው ያስረዱት። ''እያንዳንዳችን አሁን በተሰማራንበት መስክ የምናከናውነውን ተግባር፤ የምንሰራው ለምንድን ነው ብለን ልንጠይቅ ይገባል፡፡ ወደዚህ ምድር የመጣሁት ለምንድን ነው ከሚለው ጥያቄ ጀምሮ የምማረው፣ የምሰራው እና ሌሎች ነገሮችንም የማከናውነው ለምንድን ነው ለሚለው ጥያቄ ምላሽ ልታገኙ ይገባል'' ሲሉም አክለዋል በማብራሪያቸው።

እሳቸው እንዳሉት ህልማቸውን ለመኖር መኖሪያ ቤታቸውን እስከመሸጥ ደርሰዋል። ቆላ ደጋ ማስነዋል። በብዙ ውጣውረዶች ውስጥም አልፈዋል። በድንገተኛ ሕክምና ላይ የሚሰራውን ጠብታ አምቡላንስ የተሰኘውን ማህበራዊ አገልግሎት መስጫ ተቋም ለመመስረት የበቁት ከብዙ ድካም በኋላ ነው።

አቶ ክብረት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በሰመመን (አንስቴዢያ) የትምህርት መስክ መመረቃቸውን ይገልጻሉ፤ በሚወዱት በዚሁ የሙያ መስክ ህክምና ከበርካታ ሐኪሞች (ዶክተሮች) ጋር ሆነው ብዙ ቀዶ ህክምናዎችን ማድረጋቸውንና በዚህም ምስጋና እንደተቸራቸው ያክላሉ።

ማንኛውም ድንገተኛ ጉዳት የደረሰበት ሰው ትክክለኛውን የህክምና እርዳታ እያገኘ ጤና ተቋም መድረስ እንዲችል የሚያደርግ በውስጡ ዝግጁ ባለሙያዎችና የድንገተኛ ህክምና እርዳታ መስጫ መሳሪያ የተገጠመለት የአምቡላንስ አገልግሎት የመስጠት ራዕይ ነበራቸው፡ ይህን ራዕይ ለማሳካት በብዙ ውጣውረድ ውስጥ ማለፋቸውን ለመድረኩ ታዳሚዎች አስረድተዋል።እንኳንስ የገንዘብና የሞራል ድጋፍ ሊያገኙ ከጎናቸው ሆነው ያግዙኛል ብለው ተስፋ የጣሉባቸው ወዳጆቻቸው ጭምር እንደ እብድ ይቆጥሯቸው እንደነበር ያስታውሳሉ።

ሀሳባቸውን የደገፉት ባለቤታቸው መኖሪያ ቤታቸው እንዲሸጥ ተስማምተው በአንድ አምቡላንስ የጀመሩት ስራ አሁን ላይ ከ15 በሚበልጡ ዘመናዊ አምቡላንሶች የበርካታ ሰዎችን ህይወት እየታደጉ ነው። በያዙት ወረት ሳይሆን ባተረፉት ህይወት ደስተኛ መሆናቸውንም ይገልጻሉ፤ ''እያንዳንዱ ሰው የራሱን ጠብታ ካኖረ የማይቻል የለም'' ይላሉ፡፡

''ጠብታ የኔ የታለ ብሎ የመጠየቅ ፍልስፍና ነው'' የሚሉት አቶ ክብረት፣ ለዩኒቨርሲቲ ምሩቃን የምትኖሩባት ሀገር በርካታ ማህበራዊ ችግር ያለባት በመሆኗ ብዙ የስራ እድል አላትና ስራ ፈጣሪዎች እንጂ ጠባቂዎች ሳትሆኑ የየራሳችሁን ጠብታ አሳርፉ  ሲሉ ምክረ ሀሳብ ለግሰዋል።በመሰረቱት ጠብታ አምቡላንስ ማህበራዊ አገልግሎት ተቋም የራሳቸውን ጠብታ ማኖራቸውን በመግለፅ ጭምር።

ከዜጎቿ አብላጫውን የአሃዝ ድርሻ  የያዙትን ወጣቶች ይዛ ኢትዮጵያ ልትራብ፣ ልትቸገርና ልትለምን አይገባም። ኢትዮጵያ ብሎም አፍሪካ የሚስፈልጋቸው  እርዳታ ሳይሆን ለውጥ የሚያመጡ ወጣቶች ናቸው ሲሉ ነው የመከሩት። በውስጣቸው ያለውን የመስራትና የመለወጥ ኃይል ሲናገሩ የሰራሁት ይበቃኛል አለማለታቸውን፣ ወደፊት ለሀገርና ለህዘብ የመስራት ህልማቸውን ያረጋግጣል፤ የሚያነሷቸው ሀሳቦችና ገጠመኞቻቸው በአዳራሹ ያለውን አብዛኛውን ወጣት ቀልብ  የገዛ ስለመሆኑ አስረጅ አያስፈልገውም።፡

የአቶ ክብረት የስራ አጋርና 20 ዓመታትን በአውሮፓ ማሳለፋቸውን የሚናገሩት አቶ ጥበቡ አሰፋ አውሮፓውያኑ በማይመች ምድራቸው የሚመች ኑሮ ለመኖር ይጥራሉ ሲሉ ይገልጻሉ።

"እኛ ግን ገነት ውስጥ እየኖርን በድህነት የምንኖረው የዜግነት ግዴታችንን ባለመወጣታችን ነው" ይላሉ። እንደ አቶ ክብረት አይነት ሰዎች ለኢትዮጵያውያን ከፍታና መለወጥ ድርሻቸው የላቀ ነው፤ ''ሁላችንም የየራሳችንን ጠብታ ከጨመርን ኢትዮጵያ ተስፋ አላት፤ ወቅቱ ግዴታን ለመወጣት ምቹ ነው'' ብለዋል፡፡

በርካታ ዳያስቦራዎች ሀገር ቤት እንዲገቡ በተጋበዙበት በዚህ ጊዜ እያንዳንዱ ወጣት ስራ ሳይንቅ መስራት፤ ሀገራዊ አደራውን መቀበልና ሀገር በዜጋ እንደምትገነባ ማወቅ አለበት ሲሉ ለወጣቶች መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡ አቶ ጥበቡ እንዳሉት ከአውሮፓ ወደ ሀገር ቤት ተመልሰው በትምህርት ዘርፍ የመሰማራት እቅዳቸውን ለማሳካት እየሰሩ ነው።

በመድረኩ በተለያየ በጎ አድራጎት ስራ ተሳትፈው ጠብታቸውን እያሳረፉ ተቋማት በመድረኩ ድርጅቶቻቸውን ከማስተዋወቅ ባለፈ ማህበራዊ ችግሮችን በስፋት በማሳየት የተቋማቱ የስራ ዘርፍ ስራ ፈጣሪ ወጣቶችን የሚፈልግ መሆኑን አመላክተዋል፡፡

በሀገሪቱ ካሉ ዩኒቨርሲቲዎች የመጡ ተማሪዎችም የንግድ እቅዳቸውን እንዲያቀርቡ እድል ተሰጥቷቸዋል። የተሻለ የንግድ ዕቅድ ላለቸው ገንዘብ አለኝ የሚሉ የተለያዩ ባንክ ተወካዮችም ዳኞች ሆነው የንግድ እቅዱን አወዳድረዋል፡፡

የሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ መምህሩና የኢትዮጵያ ወጣቶች ትምህርትና ድጋፍ አገልግሎት በጎ አድራጎት ማህበር መስራች ረዳት ፕሮፌሰር ፍቃዱ ረታ ማህበሩ በ2012 ዓ.ም ወርሃ ግንቦት በጥቂት መምህራንና ተማሪዎች በጎ ፈቃድ የተጀመረ መሆኑን አስታውሰዋል።

የዩኒቨርሲቲ ምሩቃን ወደስራ ለመግባት የሚያጋጥማቸውን ችግር መፍታትና አዲስ የንግድ ሀሳቦችን አመንጭተው ከራስ አልፎ ሀገራዊ አበርክቶታቸውን እንዲያሳድጉ ማድረግ የማህበሩ ዋና ዓላማ መሆኑንም አመላክተዋል፡፡

በሀገሪቱ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትና ተመራቂ ተማሪዎች ቁጥር እየጨመረ ቢሄድም በዚያው ልክ ደግሞ የስራ አጥ ቁጥሩ እየበዛ በመሆኑ የስራ እድል መፍጠሩ ላይ መንግስትን ብቻ ከመጠበቅ በሚል የተጀመረ ስራ መሆኑንም ተናግረዋል።

በበጎ ፈቃድ በተጀመረው ስራ ከ10 ሺህ ለሚበልጡ ምሩቃን ወጣቶች በተለያየ የሙያ መስክ ስልጠና በመስጠት ድጋፍ የተደረገ ሲሆን፤ 2ሺህ የሚጠጉ ምሩቃን ወጣቶች ደግሞ ስራ እንዲቀጠሩ ማገዙንም ተናግረዋል፡፡

ጎን ለጎን የተለያዩ የበጎ ፈቃድ አገልግሎቶችን በመስጠት ለአረጋዊያንና ለህጻናት በበዓላት ጊዜ ድጋፍ ተደርጓዋል።

ረዳት ፕሮፌሰር ፍቃዱ እንዳሉት ''ስራ የለም'' ከሚል የስንፍና አባዜ ተላቆ በበጎ ፈቃድ ማህበረሰብን ማገልገል እንደሚቻልም ለማሳየት በሚዘጋጁ መሰል መድረኮች ላይ የበጎ አድራጎት ድርጅቶች ስራቸውን እንዲያቀርቡ እየተደረገ ነው።

''ዓላማውን የሚደግፉ ባንኮች የንግድ እቅዱን በማወዳደር በቀጣይ ለሚከናወነው ስራ ትስስር እንዲፈጠር እየተሰራ ነው'' ተመሳሳይ መድረኮች በየሶስት ወሩ ይዘጋጃሉ። መድረኮቹን በሌሎች የኢትዮጵያ ከተሞች በማድረግ የዩኒቨርሲቲ ምሩቃንን ከስራውና ከበጎ አገልግሎቱ ጋር በማገናኘት ማህበራዊ አገልግሎቱን ማጠናከር የወደፊት አቅጣጫው ነው።

ወጣት ዲቦራ በፈቃዱ በሄሳብ አያያዝ የሙያ መስክ የኮሌጅ ተመራቂ መሆኗን ትገልጻለች። በኢትዮጵያ ወጣቶችና ትምህርት ድጋፍ አገልግሎት አማካኝት የተለያዩ የህይወት ልምድ ስልጠናዎችን ወስዳለች። የወሰደችው ስልጠና ስራ እንድትቀጠር ድጋፍ አስተዋጽኦ ማድረጉን ትናገራለች። በማህበሩ ውስጥ ያላትን የበጎ ፈቃድ አገልግሎት አለማቆሟን በመጥቅስ፡፡

የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ስራ በህይወት ዘመን የሚከናወንና ከመናገር የሚበልጥ መንፈሳዊ እርካታን የሚያጎናጽፍ መሆኑን የተናገረችው ወጣት ዲቦራ፤ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ምሩቃን ግንባር ቀደም ተሳታፊ መሆን እንደሚገባቸው ምክሯን ለግሳለች፡፡ በተለያዩ ጊዜያት የሚከናወኑ ተመሳሳይ መድረኮች በተለያየ ዘርፍ ተሰማርተው ውጤታማ የሆኑ ግለሰቦችን ህይወት በማሳየት እኛስ?  የሚለውን ጥያቄ እንድንመልስ ያስቻለ ነው ብላለች፡፡

ወጣት ሕይወት ዓለሙ በበኩሏ ''አንዳንድ ሰዎች ከራሳቸው አልፈው የኛን ህይወት ለመኖር የተፈጠሩ እስኪመስለኝ ድረስ ከመድረኩ ተምሬበታለሁ'' ብላለች፡፡

እንደወጣት በተሰማራሁበት የስራ መስክ ማህበረሰቤን ማገልግልና ሀገራዊ ግዴታዬን ለመወጣት ጠብታ እንዲኖረኝ እና የማከናውናቸውን ተግባራት ለምንድን ነው ብዬ ለመጠየቅ ያስቻለኝ መድረክ ነው ስትል ገልጻለች፡፡ በንግዱ ዘርፍ ከተሰማሩ ሰዎች በተጨማሪ ኮሜዲያንና ታዋቂ ግለሰቦች በመድረኩ ላይ ተገኝተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም