በሆሳዕና ከተማ በ171 ሚሊዮን ብር የአገልግሎት መስጫ ተቋማት ግንባታ ተጀመረ

141

ሆሳዕና የካቲት 17/2014 (ኢዜአ) በሆሳዕና ከተማ በ171 ሚሊየን ብር የተለያዩ የአገልግሎት መስጫ ተቋማት ግንባታ ተጀመረ።

የአገልግሎት መስጫ ተቋማቱ ግንባታ ትላንት በይፋ ተጀምሯል።

የሆሳዕና ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ አብርሃም መጫ በስነ ስርአቱ ላይ እንዳሉት መንግስት የከተማውን ህብረተሰብ የልማት ጥያቄ ለመመለስ ተገቢውን ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ይገኛል።

የአገልግሎት መስጫዎቹ የነዋሪውን ጥያቄ መሰረት በማድረግ የሚገነቡ መሆናቸውን ጠቁመው ተቋማቱ በሶስት ወር ጊዜ ውስጥ ተገንብተው ለአገልግሎት እንደሚበቁ አመላክተዋል።

"የተቋማቱ ግንባታ በተያዘለት ጊዜ ገደብ እንዲጠናቀቅ ይደረጋል" ያሉት ከንቲባው ለተቋማቱ ግንባታ ስኬታማነት  ህብረተሰቡ በተለይም የንግዱ ማህበረሰብ ግብርን በወቅቱ ከመክፈል ጀምሮ ተገቢውን ድጋፍ እንዲያደርግ ጠይቀዋል።

የሆሳዕና ከተማ ማዘጋጃ ቤት ምክትል ስራ አስኪያጅና የከተሞች ማስፋፊያ ፕሮጀክት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አብነት አባብያ በበኩላቸው ግንባታቸው በይፋ የተጀመረው  የጌጠኛ ድንጋይ መንገዶች፣ የተፋሰስ መውረጃዎች፣ የወጣቶች መዝናኛ ማእከል፣ አረንጓዴ ስፍራዎች፣ የኤሌክትሪክ መስመር ዝርጋታ ጨምሮ 30 የተለያዩ አገልግሎት መስጫዎች መሆናቸውን ተናግረዋል።

ለአገልግሎት መስጫዎቹ ግንባታ የሚውለው በጀት በመንግስት፣በከተሞች ማስፋፊያ ፕሮግራምና በዓለም ባንክ በኩል የተመደበ መሆኑን አስታውቀዋል ።

የአገልግሎት መስጫዎቹ በከተማው በስድስት ቀበሌዎች የሚገነቡ መሆኑን አስታውቀዋል ።

በስነ ስርአቱ ላይ ከታደሙ መካከል የሄጦ ቀበሌ ነዋሪ እማሆይ በለጡ ታደሰ "በአካባቢያችን የሚገነባው የጌጠኛ ድንጋይ መንገድ ነዋሪዎች ወጥተን ለመግባት በበጋ በአቧራና  በክረምት በጭቃ  እየደረሰብን ካለው ጫና ይታደገናል" ሲሉ ተስፋቸውን ገልጸዋል ።

"የመንገዱ ግንባታ የተሳካ እንዲሆን የበኩላችንን እንወጣለን" ሲሉም ተናግረዋል ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም