የአሜሪካ መንግሥት ሕወሓትን አብቅቶለታል፤ መበተን አለበት ማለት ይገባዋል - አንጋፋው የአሜሪካ ፖለቲከኛ ኸርማን ኮኸን

70

አዲስ አበባ የካቲት 17/2014(ኢዜአ) "የአሜሪካ መንግሥት ህወሓትን አብቅቶለታል፤ መበተን አለበት ማለት ይገባዋል" ሲሉ በአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት የቀድሞ የአፍሪካ ጉዳዮች ረዳት ፀሓፊ ኸርማን ኮኸን ገለጹ።

የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ህወሓትን ከማዕከላዊ መንግሥት ጋር የሚስተካከል ቡድን አድርጎ ሲያስብ መቆየቱም የታሪክ ተወቃሽ ያደርገዋል ብለዋል።

አንጋፋ ዲፕሎማት ኸርማን ኮኸን ከአሃዱ ሬዲዮና ቴሌቪዥን የአፍሪካ ቀንድ አገልግሎት ጋር ባደረጉት ቆይታ፤ ህወሓት ሥልጣን ላይ ከወጣ ጀምሮ አምባገነናዊ ሥርዓት ማስቀጠሉንም ይናገራሉ።

ህወሓት  በቅርጽ ደረጃ በሥልጣን ላይ ያልተማከለ የፌዴራል ሥርዓት አራማጅ ሙከራ ቢያደርግም በተግባር ግን ሙሉ በሙሉ የህወሓት ማዕከላዊ አገዛዝ የተረጋገጠበት እንደነበር ገልጸዋል።

በዚህም ተግባሩ ህወሓት ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ተከታይ አለመሆኑን ነው የሚገልጹት።

ህወሓት ሥልጣን ላይ በነበረ ጊዜ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ጥቅም አለመስራቱን ጠቁመው አሁን ከፖለቲካው መድረክ ራሱን ሊያገል የሚገባ የፖለቲካ ሃይል ነው ብለዋል።

የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ህወሓት ከሥልጣን ሲወርድ ከማዕከላዊ መንግሥት ጋር እኩል አድርጎ ለማየት የሄደበት ርቀት ስህተት መሆኑንም ነው የገለጹት።

ያም ሆኖ ማዕከላዊ መንግሥት ከህወሓት ጋር ሊነጻጸር የሚችልበት ጉዳይ አለመኖሩን ገልጸው የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት እይታውን ሊያርም እንደሚገባ ጠቁመዋል።

በተለይም ደግሞ ህወሓት ያበቃለት መሆኑን ሊረዱ እንደሚገባ ነው ያስገነዘቡት።

"የአሜሪካ መንግሥት ህወሓትን አብቅቶለታል፤ መበተን አለበት ማለት ይገባዋል" ሲሉ ተናግረዋል።

ከዚህ በኋላ ህወሓት በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ስፍራ ይኖረዋል ብለው እንደማያምኑ አንጋፋው ዲፕሎማት ኸርመን ኮኸን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም