ከታላቁ የሕዳሴ ግድብ የጋራ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የታችኛው ተፋሰሱ አገራት በትብብር ሊሰሩ ይገባል

95

አዲስ አበባ የካቲት 17/2014 /ኢዜአ/ ከታላቁ የሕዳሴ ግድብ የቀጠናውም አገራት ተጠቃሚ እንዲሆኑ የታችኛው ተፋሰስ አገራት በትብብር ሊሰሩ እንደሚገባ በኢትዮጵያ የኢራን አምባሳደር ሳማድ አሊ ላኪዛዴህ ገለጹ።

በኢትዮጵያ የኢራን አምባሳደር ሳማድ አሊ ላኪዛዴህ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ኢትዮጵያ ልማቷን ለመደገፍ የምትገነባውን የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ኢራን ትደግፋለች ብለዋል።

ግድቡም ለኢትዮጵያ ሕዝብ ብቻ ሳይሆን ለጎረቤት አገራትና ለቀጠናውም ጭምር በርካታ ጥቅም እንዳለው ገልጸው ለጋራ ተጠቃሚነት በጋራ መሥራት ይገባል ብለዋል።

በተለይም የታችኛው ተፋሰስ አገራት በዚህ ረገድ በትብብር ሊሰሩ እንደሚገባ አሳስበዋል።

“ እኛ ሁሉንም የታችኛው ተፋሰስ አገራት በጋራ እንዲሰሩና እውነተኛ ውይይት እንዲያደርጉ፣ ሰላማዊ ድርድር እንዲያደርጉና ይሄ ትልቅ ፕሮጀክት ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለሁሉም የተፋሰሱ አገራት ጥቅም እንዲሰጥ እንመክራለን ብለዋል።”

ኢትዮጵያ ለሕዝቧ የኤሌክትሪክ ሃይል ለማቅረብና ዘላቂ ልማት ለማረጋገጥ በአባይ ወንዝ ላይ ግድብ የመገንባት መብት እንዳላት ጠቁመዋል።

“ ኢትዮጵያ ሃብቷን ለሕዝቡ ጥቅም ለማዋል የምታደርገውን ጥረት እንደግፋለን፤ ግድቡም ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለጎረቤትም አገራት ጭምር የሚጠቅም ነው ብለዋል።

ኢትዮጵያ አዲስ አበባን ጨምሮ ተደጋጋሚ የመብራት ሃይል መቋረጥ እንደሚገጥማት ገልጸው የግድቡም ሃይል ማመንጨት ይህንን ችግር እንደሚያቃልለው ተናግረዋል።

በአዲስ አበባ እንደሚገኝ አንድ ዲፕሎማትም በከተማዋ ያለውን የሃይል መቆራረጥ ማስተዋላቸውን ገልጸው ግድቡ ሃይል ማመንጨት መጀመሩ ትልቅ እምርታ አለው ብለዋል።

የታችኛው ተፋሰስ አገራት በውሃው የመጠቀም መብት እንዳላቸው ጠቁመው ሁሉም የተፋሰሱ አገራት ውሃውን በትብብር አልምተው መጠቀም እንደሚችሉ ገልጸዋል።

ብዙ ጊዜ ሱዳን ወይም ደግሞ ግብጽ ከፍተኛ ጎርፍ እያጋጠማቸው እንደሆነ እሰማለው፤ ስለዚህምይህ ግድብ የኤሌክትሪክ ኃይል በማቅረበ ብቻ ሳይሆን ጎርፍም በመከላከል ረገድና በተለይም ከወንዙ በሚመጡ ሌሎች አሉታዊ ተጽዕኖዎች በመከላከል ረገድ ትልቅ ጥቅም ይኖረዋል ብለዋል።

አሁን ላይ የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ከ84 በመቶ የተጠናቀቀ ሲሆን ባለፈው ሳምንት የግድቡ አንደኛው ተርባይን 375 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጨት መጀመሩ ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም