በክልሉ በአሸባሪው ህወሓት ጥቃት የደረሰባቸውን ሴቶች ለማቋቋም የድጋፍ ጥሪ ቀረበ

109

ደሴ (ኢዜአ) የካቲት 15/2014 በአማራ ክልል በአሸባሪው ህወሓት ጾታዊ ጥቃት የደረሰባቸውን ሴቶች በስነልቦና በማከም መልሶ ለማቋቋም በሚደረገው ጥረት ሁሉም የበኩሉን እገዛ እንደያደርግ የክልሉ ሴቶች፣ ህጻናትና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ጥሪ አቀረበ።
ቢሮው የተጎዱ ሴቶችን መልሶ ለማቋቋም ባለድርሻ አካላትን በማሳተፍ በቅንጅት እየሰራ መሆኑን አስታውቋል።

ቢሮው የሴቶችን ሁለተናዊ ተሳትፎ ለማሳደግና በሽብር ቡድኑ የተጎዱ ሴቶችን መልሶ ለማቋቋም በደሴ ከተማ ምክክር እያካሄደ ነው።

የክልሉ ሴቶች ህጻናትና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ አስናቁ ድረስ በመድረኩ ላይ እንደገለጹት አሸባሪው የህወሓት በክልሉ ወረራ በፈጸመበት ወቅት በሴቶች ላይ ዘግናኝና አሰቃቂ ግፍ ፈጽሟል።

"ህጻናትን ያለ አሳዳጊ፣ አረጋዊያንን ያለጧሪ ከማስቀረቱ ባለፈ ሴቶችን በአስነዋሪ ሁኔታ በቡድን ጭምር በቤተሰብ ፊት ደፍሯል፤ ገድሏል፤ የተለያየ ጾታዊ ጥቃትም ፈጽሟል" ሲሉ ተናግረዋል።

በተደረገ የዳሰሳ ጥናት ከ800 የሚበልጡ ሴቶች ላይ ፆታዊ ጥቃት መፈጸሙ እና ከ2 ሺህ የሚበልጡ ሴቶችን መኖሪያ ቤት ማቃጠሉ መረጋገጡን ጠቅሰዋል።

ኃላፊዋ እንዳሉት ከፌደራል መንግስት ጋር ፕሮጀክት ተቀርጾ ቅድሚያ ለሚሰጣቸው 1ሺህ 590 ቤቶችን በተሻለ ሁኔታ ለመገንባት ልየታ ተደርጎ ወደ ስራ ተገብቷል።

የቤት ግንባታው በወልድያ ከተማ መጀመሩንና እስካሁንም አምስት ቤቶች በተሻለ ሁኔታ መሰራታቸውን አመልክተዋል።

ከእዚህ በተጨማሪ ዳያስፖራውንና ድርጅቶችን በማስተባበር በጦርነቱ ለተቸገሩ ከ112 ሺህ ለሚበልጡ ሴቶች 326 ሚሊዮን ብር ድጋፍ መሰራጨቱን ወይዘሮ አስናቁ ገልጸዋል።

የተጎዱ ሴቶችን በስነ ልቦና በማከም መልሶ ለማቋቋም ባለድርሻ አካላትን በማሳተፍ በቅንጅት እየተሰራ መሆኑንም ነው ያመለከቱት።

"ከደረሰባቸው የስነ ልቦና ጫና ለማላቀቅም ስልጠና፣ ሕክምናና ሌሎች ድጋፎች እየተደረላቸው ሲሆን ይህም ተጠናክሮ ይቀጥላል" ሲሉ አስታውቀዋል።

የተጎዱ ሴቶችን በስነ ልቦና በማከም በማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና በሌሎች ዘርፎች ለመደገፍ በሚደረገው ጥረት ሁሉም የድርሻውን እገዛ እንዲያደርግ ኃላፊ ጥሪ አቅርበዋል።

የኮምቦልቻ ከተማ አስተዳደር ሴቶች ህጻናትና ማህበራዊ ጉዳይ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ወይዘሮ ዘሪቱ ሁሴን በበኩላቸው፣ በሽብር ቡድኑ ጾታዊ ጥቃት የደረሰባቸውን ሴቶች መልሶ ለማቋቋምና በስነ ልቦና ለማከም እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

እስካሁን ለ35 ሴቶች የገንዘብና የቁሳቁስ ድጋፍ መደረጉን ጠቁመው፣ ከችግሮቻቸው እንዲወጡ ቅንጅታዊ ስራው ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አመለክተዋል።

በብልፅግና ፓርቲ የአማራ ክልል ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ግርማ የሽጥላ በበኩላቸው "አሸባሪው ህወሓት ኢትዮጵያን ለማፍረስ ያልፈጸመው በደልና ግፍ የለም" ብለዋል።

የሽብር ቡድኑ ያደረሰውን ሁለንተናዊ ጉዳት ክልሉ ተቋቁሞ የመልሶ ግንባታ ሥራ መጀመሩን ጠቁመው፤ በተለይ በሴትና ህጻናት ላይ ያደረሰው ጉዳት ጊዜ የማይሰጥ ቀዳሚ አጀንዳ መሆኑን ገልጸዋል።

ለሁለት ቀናት በሚቆየው የምክክር መድረክ ላይ ከክልልና ከተለያዩ ዞኖች የተውጣጡ አመራሮችና ባለድርሻ አካላት እየተሳተፉ ነው ሲል የዘገበው ኢዜአ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም