ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ማብራሪያ የመንግስትን አቋም መረዳት ችለናል- ነዋሪዎች

50

ሀዋሳ የካቲት 15/2014 (ኢዜአ) ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ለቀረበላቸው ጥያቄ የሰጡት ማብራሪያ የመንግስትን አቋም እንድንገነዘብ ረድቶናል ሲሉ አስተያየታቸውን የሰጡ የሀዋሳ ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ ።
የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ዛሬ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 3ኛው አስቸኳይ ስብሰባ ተገኝተው በወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

ኢዜአ ካነጋገራቸው የሀዋሳ ከተማ ነዋሪዎች መካከል በግንባታ ስራ መሰማራታቸውን የሚናገሩት አቶ ዮናስ ማቴዎስ፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ኢትዮጵያ በቀጣይ በልማት ጎዳና ጎልታ መውጣት እንድትችልና ዜጎች ተጠቃሚ እንዲሆኑ በየተሰማሩበት ጠንካራ ሰራተኛ መሆን እንደሚገባ ያቀረቡት አስተያየት ልዩ ቦታ የሚሰጡት መሆኑን ገልጸዋል።

የገበያ ስርዓቱን እያዛቡ የሚገኙ የቀድሞ ስርዓት ርዝራዦችና በህገ ወጥ መንገድ ተጠቃሚ የነበሩ እጃቸው ያለበት ስለመሆኑ መረዳታቸውን ገልጸው በጉዳዩ ዙሪያ የተሰጠው ማብራሪያ ህዝቡ ድርጊቱን ለመከላከል  ከመንግስት ጎን እንዲቆም የሚያደርግ መሆኑን አመላክተዋል።

በተለያዩ ምክንያቶች ግንባታው በመጓተቱ ቅሬታ ሲፈጥርና በመንግስት ላይ ዕምነት ሸርሽሮ የነበረው ታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታው እንዲፋጠንና ሀገር ለመውረር ከውጭ ጠላት ጋር በማበር ህወሓት ያወጀውን ጦርነት ለመመከት በግንባር በመሰለፍ ያሳዩት ቁርጠኝነት ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ያለንን ድጋፍ እንድናጠናክር ያደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

"ጠቅላይ ሚኒስትሩ በወንጀል ተጠርጥረው የታሰሩ ግለሰቦች መፈታትን በተመለከተ በሰጡት ማብራሪያ ለሀገር ብሄራዊ ጥቅም ሲባል የተደረገ የመንግስት አቋም መሆኑን መረዳት ችያለሁ" ብለዋል።

በየመንግስት ተቋማት በገንዘብ እየተሸጠ ያለ አገልግሎት አሰጣጥ ተገቢ መስመር እንዲይዝ ሌብነትና ሙስናን ለመከላከል በቀጣይ የተያዘው አቋም የለውጡ ምዕራፍ ላይ የነበረውን ብዥታ ያጠራ መሆኑን ከማብራሪያው መገንዘባቸውን ገልጸው ለውጡ ተጠናክሮ እንዲቀጥልና ግቡን እንዲመታ ጠንካራ ድጋፍ እንደሚያደርጉ አስታውቀዋል።

ሌላው አስተያየቱን የሰጠው በሀዋሳ ሀይቅ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የ10ኛ ክፍል ተማሪ ጽኑቃል ዮናስ፤ እንደሀገር ያስቀመጥናቸውን ግቦች ለማሳካት ይቅርታ ወሳኝ መሆኑን ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ማብራሪያ መረዳቱን ተናግሯል።

This image has an empty alt attribute; its file name is image-15.png

ህዝቡ በኑሮ ውድነትም ሆነ ከመንግስት ከሚፈለጉ በተለያዩ አገልግሎቶች እንዲማረርና በመንግስት ላይ ዕምነት እንዲያጣ እየተሰሩ ያሉ ስውር ዓላማ ያላቸው ግለሰቦች እንዳሉ ከማብራሪያው መረዳቱን የገለጸው ወጣቱ "ህዝቡ በቂ ድጋፍ ማድረግ አለበት" ብሏል።

የጠቅላይ ሚኒስትሩን ማብራሪያ በቁም ነገር ጊዜ ሰጥተው ማዳመጣቸውን የገለጹት አቶ እንዳሻው ካምባታ በበኩላቸው በተለያዩ ምክንያቶች የተፈጠሩ ቁርሾዎችን ለማስወገድና ዘላቂ ሰላም ለመፍጠር ብሄራዊ ምክክርና ዕርቅን መጠቀም እንደሚገባ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያነሱት ሀሳብ ቀልባቸውን እንደሳበ አመላክተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ የያዙት አቋምና ራዕያቸው የሀገራችንን የቀደመ ዝናና ሀያልነት ለመመለስ መሆኑን እንረዳለን ያሉት  አቶ እንዳሻው "ከውስጥ የተሰገሰጉ እንቅፋት ፈጣሪዎችን ለማጥራት መታገዝ ይገባቸዋል" ብለዋል።

ሀገር በህልውና ጦርነት በገባችበት ወቅት ኑሮን በማስወደድ በተለይም በትራንስፖርት ዘርፍ ካለምንም ከልካይ ዋጋ እየጨመሩ ህዝብ የሚያስመርሩ አካላት እንዳሉ ከማብራሪያው መገንዘባቸውን ገልጸዋል።

መንግስት በቀጣይ በልማትና በዴሚክራሲ ግንባታ የሰጠው ትኩረት የተጀመረውን ለውጥ የሚያጠናክር በመሆኑ ቀጣይነት ያለው ድጋፍ እንደሚያደርጉ አቶ እንዳሻው አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም