ጤና ቢሮው በደቡብ ወሎ በአሸባሪው ቡድን የወደሙ ጤና ተቋማትን ለማቋቋም ከ9 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት ድጋፍ አደረገ

100

ደሴ የካቲት 15/2014 (ኢዜአ ) የደቡብ ክልል ጤና ቢሮ በአሸባሪው ህወሓት ቡድን በደቡብ ወሎ ዞን የወደሙ ጤና ተቋማትን መልሶ ለማቋቋም የሚውል ከ9 ሚሊየን ብር በላይ ግምት ያለው መድኃኒትና የህክምና ቁሳቁስ ድጋፍ አደረገ፡፡
የደቡብ ክልል ጤና ቢሮ ኃላፊ አቶ እንደሻው ሽብሩ ድጋፉን ዛሬ ባስረከቡበት ወቅት እንደገለጹት አሸባሪው ህወሓት ያደረሰውን ሁለንተናዊ ጉዳት በጋራ መመከትና የወደሙ ተቋማትን በትብብር መልሶ ማቋቋም ያስፈልጋል፡፡

ቢሮው የችግሩን ስፋት በመረዳት በቡድኑ የወደሙ ጤና ተቋማትን መልሶ ለማቋቋም እየተደረገ ያለውን ጥረት ለማገዝ  ከ9 ሚሊዮን ብር በላይ ግምት ያለው መድኃኒትና የህክምና ቁሳቁስ  ዛሬ ድጋፍ ማድረጉን ተናግረዋል፡፡

ቢሮው በጦርነቱ የወደሙ ሰባት ሆስፒታሎችን በዘላቂነት መልሶ ለማቋቋም የተለያየ ድጋፍ እያደረገ መሆኑን አስታውቀዋል።

የደቡብ ወሎ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አብዱ ሁሴን በበኩላቸው በዞኑ በሽብር ቡድኑ የወደሙ ተቋማትን መልሶ ለማቋቋም ከባለድርሻ አካላት ጋር በትብብር  እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

"አሸባሪው ህወሓት በተለይ ጤና ተቋማት ላይ ካደረሰው ውድመት አንጻር በቀላሉ ማስተካከል ባለመቻሉ ለህብረተሰቡ በሚፈለገው ልክ የጤና አገልግሎት መስጠት አልተቻለም" ብለዋል፡፡

በቢሮው የተደረገው ድጋፍ በዋናነት የድንገተኛና የእናቶችን የወሊድ አገልግሎቶች ለመስጠት እንደሚያግዝ ጠቁመው ለተደረጋው ድጋፍ አመስግነዋል።

አሸባሪው ህወሓት በዞኑ ወረራ በፈጸመበት ወቅት 101 ጤና ጣቢያዎች፣ ሰባት ሆስፒታሎችና 398 ጤና ኬላዎችን መዝረፉንና ማውደሙን የተናገሩት ደግሞ የደቡብ ወሎ ዞን ጤና መምሪያ ኃላፊ አቶ ጌታቸው በለጠ ናቸው።

የወደሙ ጤና ተቋማትን በቅንጅት መልሶ በማቋቋም በከፊል አገልግሎት እንዲሰጡ እየተደረገ መሆኑን አመላክተዋል።

ተቋማቱ በደረሰባቸው ውድመት በሙሉ አቅማቸው ስራ መጀመር እንዳልቻሉ ጠቁመው "ሆስፒታሎች ከጤና ጣቢያ ደረጃ በታች ለመስራት የተገደዱበት ሁኔታ ተፈጥሯል" ነው ያሉት፡፡

የጤና ተቋማትን መልሶ በማደራጀት አገልግሎት እንዲሰጡ ለማስቻል እየተደረገ ባለው ጥረት ሁሉም በሚችለው ድጋፍ እንዲያደርግ ጠይቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም