አዲስ ተሿሚ አምባሳደሮች ተልዕኳቸውን በብቃት ለመወጣት በትኩረት መሥራት አለባቸው

90

የካቲት 15 ቀን 2014 (ኢዜአ) አዲስ ተሿሚ አምባሳደሮች የተሰጣቸውን ተልእኮ በብቃት ለመወጣት በትኩረት መሥራት እንዳለባቸው የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ዴኤታ አምባሳደር ብርቱካን አያኖ አሳሰቡ።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በተለያዩ አገራት ለተመደቡ አዲስ ተሿሚና ነባር አምባሳደሮች ለተልዕኮ እንዲዘጋጁ የሚያስችል ሥልጠና ዛሬ ተጀምሯል።

የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ዴኤታ አምባሳደር ብርቱካን አያኖ ለአምባሳደሮቹ ባስተላለፉት መልዕክት አምባሳደሮች የአገሪቱን እውነታ ለተወከሉበት አገር ማስገንዘብ አለባቸው ብለዋል።

የዲፕሎማሲው የዓለም አቀፍ ግንኙነት መስኩ ተለዋዋጭ መሆኑን አንስተው፤ አምባሳደሮቹ ከዚህ ተለዋዋጭ ሁኔታ ጋር እኩል ለመራመድ ራሳቸውን ማብቃት እንዳለባቸው አሳስበዋል።

ኢትዮጵያ ያለችበት ቀጠና የበርካታ ሃያላን አገራት ዓይን ማረፊያና የብሔራዊ ጥቅማቸው የስበት ማዕከል መሆኑን ገልጸው፤ በአካበቢው ያለውን ጂኦ-ፖለቲካ ለውጥ በአንክሮ እንዲከታተሉት ተናግረዋል።

ይህንንም ተከትሎ አዲስ ተሿሚ አምባሳደሮች በተወከሉበት ሚሲዮኖች የተሰጣቸውን ተልዕኮ በብቃት ለመወጣት መዘጋጀት እንዳለባቸው ነው ሚኒስትር ዴኤታዋ ያስገነዘቡት፡፡

የአምባሳደርነት የሥራ ዘርፍ የአገራት ብሔራዊ ጥቅሞች እንዲረጋገጡ የሚወሰንበት ከፍተኛ የሥልጣን እርከን መሆኑን በመገንዘብ ተግባራዊ እንቅስቃሴ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል።

አምባሳደሮች አሁን ኢትዮጵያ ካለችበት ወቅታዊ ሁኔታ አንጻረም ትልቅ ኃላፊነት እንዳለባቸው በመገንዘብና ቀን ከሌሊት ሊሰሩ እንደመገባም ነው የገለጹት።

ለአስራ አምስት ቀናት በሚቆየው የአምባሳደሮች ሥልጠና፤ የተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ከነባራዊ ሁኔታዎች ጋር በማሳያዎች እየተመሳከሩ ስልጠና እንደሚሰጥ ጠቁመዋል።

አምባሳደሮቹ በበኩላቸው የኢትዮጵያን የሁለትዮሽ ግንኙነት የማጠናከር፣ ብሔራዊ ጥቅም የማስከበር፣ በአገር ገጽታ ግንባታና በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ትክክለኛውን ሁኔታ የማሳወቅ ሥራ እንደሚሰሩ አረጋግጠዋል።

ሥልጠናው በኢኮኖሚ፣ በፖለቲካና በዜጋ ተኮር ዲፕሎማሲ እንዲሁም በአገር ገጽታ ግንባታ፣ በዲጂታል ዲፕሎማሲና በቆንጽላ አገልግሎት ላይ ያተኮረ ነው ተብሏል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም